ቀጥታ፡

አገልግሎቱ በመረጃ አሰባሰብና አደረጃጀት ላይ የታዩበትን ክፍተቶች ለማረም የድርጊት መርሃ ግብር እንዲያቀርብ ምክር ቤቱ አሳሰበ

ጥር 23 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት በመረጃ አሰባሰብና አደረጃጀት ላይ የታዩበትን ክፍተቶች ለማረም የሚያስችል የድርጊት መርሃ ግብር በቀጣዮቹ አራት ቀናት እንዲያቀርብ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጭ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ቀደም ሲል ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጄንሲ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የተባለውን ተቋም የ2012/13 የክዋኔ ኦዲትን በተመለከተ ህዝባዊ ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ በፈረመችው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሰረት የምታከናውናቸውን የዘላቂ ልማት ግቦች በተመለከተ ተነስቷል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ከመረጃ አሰባሰብና አደረጃጀት አንፃር ውስንነቶች ያሉበት መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው የኦዲት ግኝቱን መሰረት በማድረግ ገምግሟል።

አገልግሎቱ ከአገራዊ የመረጃ ማሰባሰብና ማደራጀት ተልዕኮውን ለመፈፀም ወጥነት ያለው፣ የተደራጀና ግልፅ የመረጃ አሰባሰብና አደረጃጀት ስርዓት እየተከተለ አይደለም ተብሏል።

በየጊዜው በሚዘጋጁ አገራዊ መረጃዎች ላይ የዘላቂ ልማት ግቦችን በተመለከተ እንደ አገር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለይቶ በማስቀመጥ ውስንነት ያለበት መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ተመልክቷል።

በመሆኑም አገልግሎቱ ያሉበትን ክፍተቶች ለመሙላት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

አገልግሎቱ የአፈፃፀም ጉድለቱን ለማረምና ለማስተካከል በቀጣዮቹ አራት ቀናት (እስከ ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም) ድረስ የድርጊት መርሃ ግብር እንዲያቀርብ መመሪያ ተሰጥቷል።

አገልግሎቱ ለሚያደርገው የስራ እንቅስቃሴ እንቅፋት የሆኑ ህጎችና አሰራሮች ካሉ ወይም በህግና በአሰራር መደገፍ ያለባቸው ችግሮች ካሉ ለይቶ ያቅርብ ተብሏል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴርም በስሩ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት በመከታተልና በመደገፍ የታዩበት ጉድለቶች እንዲፈቱ ማድረግ አለበት ብሏል ቋሚ ኮሚቴው።

የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ፤ በኦዲት ግኝቱ ላይ የቀረቡትን ጥያቄና አስተያየቶች በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተለይ ከተቋማት ጋር ወጥ የሆነ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ከማድረግ አኳያ ስምምነቶችን ወደ ተግባር የሚቀይር ህግ የሚያስፈልግ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዘላቂ ልማት ግቦችን የሚመለከቱ መረጃዎችን ለይቶ ከማደራጀት አኳያ የታዩበትን ጉድለቶች ያስተካክላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ከአሁን በፊት የነበረውን የመረጃ ተደራሽነት የማስፋት ስራ ይከናወናልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም