በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚሳተፍበት የ"ኑ ቡና ጠጡ " ስነ ስርአት ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚሳተፍበት የ"ኑ ቡና ጠጡ " ስነ ስርአት ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል

አዳማ፣ ጥር 23/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያዊያንን የ"ኑ ቡና ጠጡ" ባህል ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ከ5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚሳተፍበት ስነ ስርአት መዘጋጀቱን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የቡና መገኛ መሆኗንና የዜጎቿን እንግዳ ተቀባይነት ማሳያ የሆነውን የ"ኑ ቡና ጠጡ" ባህል ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ ዝግጅት ተደርጓል።
ዝግጅቱ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን የአብሮነትና የመቻቻል ባህልና እሴት ለማስተዋወቅ ከመሆኑም ባለፈ የቡና ልማትና የምርት ጥራትን ማስጠበቅ ላይ ማህበረሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ጭምር እሳቤ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ቡና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑን ዜጎች ተገንዝበው በዘርፉ ልማት፣ በምርቱ የእሴት ሰንሰለትና ተቀባይነት ላይ በትኩረት እንዲሰሩ በብሄራዊ ደረጃ የቡና እንጠጣ ቀን ስያሜ ለመስጠት ጭምር አላማ ያደረገ አገር አቀፍ የ"ኑ ቡና ጠጡ" ስነ ስርአት የካቲት 6 ቀን 2014 ዓ.ም ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል ።
ስነ ስርአቱ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል በየደረጃው ባሉ አደረጃጀቶች እንደሚካሄድ ጠቁመው በስነ ስርአቱ ላይ የሚሳተፈውን የህዝብ ብዛት በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ የማስመዝገብ ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያዊያን የቡና አፈላል ባህልና እውቀት የሚተዋወቅበት መሆኑንም አመልክተዋል ።
ዝግጅቶቹ በሚካሄዱባቸው ስፍራዎች ህዝባዊ ስፖርቶችና ውድድሮች፣ ሩጫዎች፣ የገመድ ጉተታ፣ የፈረስ ጉግስና ሌሎች ኩነቶችና ትርኢቶች እንደሚከናወኑ ጠቅሰዋል።
"ዕለቱ የኢትዮጵያን ቡና በዓለም የምናስጠራበትና የቡና ምርቷን ዝናም የምናሳውቀበት ይሆናል" ሲሉ አመላክተዋል።
ከፌዴራል እስከ ክልል በየደረጃው ያለው አመራር እንዲሁም ህብረተሰቡ በስነ ስርአቱ ከመሳተፍ ባለፈ ለዝግጅቱ ስኬታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ሚኒስትር ዴኤታዋ መልእክት አስተላልፈዋል ።