የኅብረቱ ጉባዔ በመዲናዋ መካሄድ ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኅብረቱ ጉባዔ በመዲናዋ መካሄድ ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው
ጥር 23/2014/ኢዜአ/ በአዲስ አበባ የሚካሄደው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ገጽታ የማጠልሸት ፕሮፖጋንዳን የቀየረ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የሕግ ምሁር ዶክተር አልማው ክፍሌ ገለጹ።
ዶክተር አልማው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነጮች አፍሪካዊያንና ሌሎች ጥቁር ሕዝቦችን በቅኝ ግዛት ተቀራምተው ከፍተኛ ሠብዓዊ ብዝበዛ ማካሄዳቸውን አስታውሰዋል።
በወቅቱም ጥቁሮችን እንደ ሰው ባለመቁጠር ገበያ ላይ እንደ እቃ ይሸጡ፤ ይለውጡ እንደነበረም እንዲሁ።
ኢትዮጵያ ይህንን አስተሳሰብ በመቀየር በቅኝ ግዛት የጭቆና ቀንበር ስር ይኖሩ ለነበሩ አፍሪካዊያንና ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ፋና ወጊ በመሆን የትግል መስራችና ምልክት መሆኗን አውስተዋል።
የአድዋ ድል የነበረውን አስተሳሰባዊ ስነ-ልቦና ሰባብሮ በመጣል ጥቁር ሕዝቦች በማንነታቸውና በቋንቋቸው እንዲኮሩ በማድረግ ሰው የመሆን ተፈጥሯዊ ጸጋቸውን በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የአፍሪካዊያን አንድነት ሥርዓት እንዲበጅለት በማሰብ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ጉልህ ሚና መጫወቷን በመጥቀስ።
ዶክተር አልማው በአፍሪካ የነበረውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሽኩቻ በማሸነፍ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪዎችና የዲፕሎማሲ ሰዎች ብቃትና ክህሎት የተሞላበት የዲፕሎማሲ ስራ ሰርተው ማለፋቸውን ጠቅሰዋል።
አሁንም የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ስኬት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማሳየት ዘርፈ ብዙ መልዕክት ያስተላልፋል ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ተሳክቶላታል" የሚሉት ዶክተር አልማው አፍሪካዊያንን ጠርቶ ጉባኤውን ማካሄድ መቻሉ እየተስተዋለ ያለውን ጫና በማክሸፍ ለኢትዮጵያና ለአመራሮቿ ትልቅ ስኬት እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ምሁሩ አፍሪካዊያንም ወደ አንድ ኅብረት በመምጣት የመሰረተ ልማት ትስስር ፈጥረው አንድ የመገበያያ ገንዘብ ለመጠቀም ያስቀመጡትን ራዕይ እውን የማድረጊያቸው ጊዜ አሁን ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በጉባኤው መሰባሰባቸውም "የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካዊያን" መፍታት እንደሚቻል በማሳየት ነጮች ለሚያራምዱት የተመፅዋችነት ስነ-ልቦና በቃችሁ የሚል መልዕክት ያስተላልፋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሠላም አይደለችም፣ ፈርሳለች፣ አትሂዱ፣ ወጥታችሁ አትገቡም በማለት የሚራገበውን ገጽታ የማጠልሸት ተግባር ለማክሸፍ ጉባኤው ስኬታማና ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንግዶችን በተገቢው መንገድ አስተናግዶ መሸኘት እንደሚገባም ዶክተር አልማው መክረዋል።
ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ የሚካሄደውን 35ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ለመታደም እንግዶች ከትናንትና ጀምሮ አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል።