ቀጥታ፡

ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የማህበረሰቡ የሠላም እሴቶችን ማበልፀግና መጠቀም ይገባል-የሠላም ሚኒስቴር

ሀዋሳ ጥር 23/2014(ኢዜአ)ብሔራዊ መግባባትና ሠላምን ለማስፈን በማህበረሰቡ ውስጥ የሠላም ግንባታ እሴቶችን በማበልፀግ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር አሳሰበ።

የሰላም ሚኒስቴር ከሲዳማ ክልል ጋር በመተባበር የፌዴራልና የክልል የሠላምና ፀጥታ አካላት የጋራ የምክክር መድረክ በሀዋሳ አካሂዷል፤

በመድረኩ በሠላም ፖሊሲና ማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች ረቂቅ ሰነድና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል።

የሠላም ሚኒስቴር የሠላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ ሠላም ፖሊሲና ማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች ረቂቅ ሰነድ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ሠነዱ የኢትዮጵያ ሠላም ግንባታ በፖሊሲና ስትራቴጂካዊ ታክቲኮች ተደግፎ በዕቅድ እንዲመራ እንደሚያደርግ ተናግረዋል ።

ሰነዱ በተለያዩ ደረጃዎች ባለሙያዎች ተወያይተውበት ግብዓቶች እንደተሰበሰበበትም አስታውቀዋል ፡፡

"የፖሊሲው ዋንኛ ማጠንጠኛም አገር በቀል የሠላም እሴቶችን ማጎልበትና በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ማዋልን መሠረት ያደርጋል" ብለዋል፡፡

ለዚህም ማህበራዊ የሠላም እሴቶች ለብሔራዊ መግባባትና ለአገራዊ አንድነት የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ የጎላ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።

የማህበራዊ እሴቶችን ፋይዳም በተመለከተ ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ግጭቶች ፤ በባህላዊ መንገድ ሲበርዱና እርቅ ሲወርድ በሁለቱም ወገኖች መካከል ከቀድሞው የበለጠ ፍፁም ወዳጅነትና ዝምድና እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ለሠላም ግንባታና ለአብሮነት ከፍተኛውን ትኩረት በመስጠት አንድነቷ የተረጋገጠና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

በኢትዮጵያ ለማካሄድ የታሰበው ሁሉን አካታች የሆነ አገራዊ የምክክር መድረክ ከነዚህ ተግባራት በዋናነት ተጠቃሽ እንደሆነም አስረድተዋል።

"ለቀጣዩ ትውልድ ቂምና ቁርሾን ሳይሆን፤ አብሮነትና መተባበርን ለማስረከብ ሁላችንም ለሠላም መክፈል የሚገባንን ዋጋ ሁሉ መክፈል ይጠበቅብናል" ብለዋል አቶ ደስታ፡፡

''ኢትዮጵያዊያን በየባህላችን ችግሮቻችንን ተነጋግረን የምንፈታበት የሠላም እሴት ያለን ህዝቦች ነን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ከአባቶች የወረስናቸውን እነዚህን እሴቶች በመጠቀም በይቅርታና ፍቅር አገርን ማሻገር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በሀገር ደረጃ ያሉ አለመግባባቶችን በሰከነ መንገድ በመፍታት ብሔራዊ መግባባትና ሠላም መፍጠር እንደሚያሻ አስረድተው፣ ለዚህም የማህበረሰብ የግጭት አፈታትና የሠላም ግንባታ እሴቶችን ማበልፀግና ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል ፡፡

የሠላም ግንባታ ሥራው በፖሊሲና ስትራቴጂ መመራቱ ለአካታች አገራዊ ምክክር መድረኩም ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ከዚህ በፊት በነበሩ የፖለቲካ አሻጥሮች የሲዳማ ህዝብ በውስጥም ሆነ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ላይ ለሠላም እጦት ተዳርጎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

"ክልሉንና አካባቢውን ወደ ሠላማዊ እንቅስቃሴ ማምጣት የተቻለው በተለይ በደቡብና በኦሮሚያ ክልልች አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉትን የጋራ የሠላም እሴቶቻችንን ተጠቅመን ነው" ብለዋል ፡፡

ማህበራዊ ሀብቶችን በማጎልበት ለዘላቂ ሠላምና አንድነት ጥቅም ላይ ለማዋል ቢሮው በትኩረት እንደሚሰራ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

በአካባቢዎቹ በነበሩ አለመግባባቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ከ69 ሺህ በላይ ዜጎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የጋራ ባህላዊ እሴቶችንና የህዝብ ለህዝብ መድረኮችን በመጠቀም ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ ላይ ሠላም ሚኒስቴርና የክልሎች የሠላምና ፀጥታ ዘርፍ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች የፌዴራልና የክልል አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም