ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ተሳታፊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ እየገቡ ነው

ጥር23/2014/ኢዜአ/ የአፍሪካ ህብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ተሳታፊ የሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ እየገቡ ነው።

የዚምባቡዌ እና የሳኦ ቶሜና ፕሪንሲፔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል።


በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና በ40ኛው የአፍሪካ ህብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ለመካፈል የተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ እየገቡ ነው።

ከተሳታፊዎች መካከል የዚምባብዌ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ፍሬድሪክ ሻቫ እና የሳኦ ቶሜና ፕሪንሲፔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤዲቴ ዶ ራሞስ ዳ ኮስታ ቴን-ዡዋ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ዋና ሹም አምባሳደር ፈይሰል አሊ ተቀብለዋቸዋል።

May be an image of 2 people, people sitting and indoor

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና በ40ኛው የህብረቱ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ለመካፈል አዲስ አበባ መግባት መጀመራቸውን አምባሳደር ፈይሰል ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ እንግዶቿን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጓን ገልጸው በሚቀጥሉት ተከታታይ ቀናት ሁሉንም እንግዶቻችንን እንቀበላለን ብለዋል።

በጉባኤው ላይ 44 አባል አገራት በአካል ተገኝተው እንደሚሳተፉ ያሳወቁት አምባሳደር ፈይሰል ኢትዮጵያ ለመስተንግዶው ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን በጥሩ ዝግጅትና መስተንግዶ ለማካሄድ በሁሉም መስክ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ እስካሁን የ25 የአፍሪካ አገራት መሪዎች እንደሚገኙ የተረጋገጠ ሲሆን የተወሰኑ አገራት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው የሚወከሉ ይሆናል።

በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ ሌሎች አገራትም ዛሬና ነገ እንደሚያሳውቁ ይጠበቃል ብለዋል አምባሳደር ፈይሰል።

የአፍሪካ ወንድምና እህቶች የኢትዮጵያን የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ በደንብ ተገንዝበውና እምነት አሳድረው ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰናቸውን አስታውሰዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያ በቂ ዝግጅተ አድርጋ እንግዶቿን በመቀበል ላይ ትገኛለች ብለዋል።

ለጉባኤው ስኬታማነት እንግዶችን ከመቀበል ጀምሮ ለሰላማዊ ሂደቱ ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የፊታችን ቅዳሜና እሁድ የሚካሄድ ሲሆን 40ኛው የህብረቱ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ቀደም ብሎ ረቡዕ እና ሐሙስ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም