አሸባሪው ህወሓት ዳግም ለሀገር ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት ዳግም ለሀገር ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ ይገባል
ደሴ፣ ጥር 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ ያካሄደውን ትግል አጠናክሮ በማስቀጠል አሸባሪው ህወሓት ዳግም ለሀገርና ሕዝብ ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ እንደሚገባ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ አሳሰቡ።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ በሕልውና ዘመቻው የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱና መስዋዕትነት ለከፈሉ የሠራዊት አባላት፣ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የዕውቅና እና የምስጋና መርሃግብር በወልድያ ከተማ ዛሬ አካሂዷል።
የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዞር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ በሥነሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የነበረው ህልም ከሽፏል።
ህዝቡ ከመከላከያ ሠራዊቱና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጎን በመሰለፍ ባደረገው ትግል በአጭር ቀን አንጸባራቂ ድል ማስመዝገቡን አስታውሰው፤ ህዝቡ ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ የሽብር ቡድኑ ዳግም ለህዝብና ሀገር ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በፅናት መታገል አለበት ብለዋል።
ሠራዊቱም ተራራ፣ በረሃ፣ ዝናብና ብርድ ሳይበግረው የሽብር ቡድኑን እግር በእግር ተከታትሎ በመደምሰስ መንግሥትንና ህዝብን ያኮራ ድል ማስመዝገቡን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ሳይንሳዊ የውትድርና ስልቶችን በመጠቀም በአጭር ጊዜ ያስመዘገበው ድል በመልካም ተሞክሮነት ተቀምሮ ለሌላ ጊዜ ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።
"አሁን ላይ የሽብር ቡድኑ ያደረሰው ውደመትና ጥቃት ተመክቷል" ያሉት ጀነራሉ፤ የሽብር ቡድኑን ለመጨረሻ ጊዜ በጋራ መቅበር ይጠበቅብናል ብለዋል።
የዛሬው የምስጋና እና የዕውቅና መርሃ ግብር በተገኘው ድል እንዲያኩራራ ሳይሆን ለቀጣይ ግዳጅና ተልዕኮ የሚያነሳሳ መሆን በመገንዘብ ራስን ሁልጊዜም ለላቀ ድል ማዘጋጀት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌፍትናንት ጀነራል ሰለሞን ኢተፋ በበኩላቸው ዕዛቸው በተሰለፈባቸው አውደ ውጊያዎች የአሸባሪውን ቡድን ፍላጎት ያከሸፈ በታሪክ የማይረሳ ገድል ፈጽሟል ብለዋል።
በቅንጅት በሰጡት በሳል አመራር ሠራዊቱ ብልሃት በተሞላበት ወታደራዊ ጥበብ በፈጸመው ተከታታይ ማጥቃት ጠላት በተራራና በአርሶ አደር መሬት ላይ የቆፈረውን ምሽግ ጥሎ እንዲፈረጥጥ አድርጎታል።
በዚህም ከፍተኛ ተጋድሎና አስተዋጽኦ ላበረከቱ ክፍለ ጦሮች፣ አመራሮች፣ የሠራዊት አባላት፣ ተቋማትና ሌሎች አካላት ዛሬ ዕውቅና እና ምስጋና መሰጠቱ ለበለጠ ድል የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።
ዕውቅና መሰጠቱ ህብረተሰቡንና ሠራዊቱን ለማነቃቃትና ለቀጣይ ተልዕኮ ለማነሳሳት ይጠቅማል ያሉት ዋና አዛዡ በቀጣይም ሀገርና ሕዝቡን ከስጋት ለመታደግ መዘጋጀት እንደሚገባ እስገንዝበዋል።
ዕውቅና እና ሽልማት ከተሠጣቸው መካከል ኮሎኔል አየለ ቢፍቱ በሰጡት አስተያየት ባገኙት ዕውቅና እና ሽልማት ሳይኩራሩ ጠንክረው በመስራት ሀገርንና ህዝብን ከሽብር ቡድኑ ስጋት ነፃ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በመርሃግብሩ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባን ጨምሮ ሠራዊቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ አመራሮችና አባላት፣ እንዲሁም የኃይማኖት አባቶችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።