ቀጥታ፡

ተተኪ ጀግና ለመፍጠር ለሀገር ክብርና ሕልውና መስዋዕትነት የከፈሉትን ማስታወስ ወሳኝ ነው

ሆሳዕና፣ ጥር 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለሀገር ክብርና ሕልውና መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን ማስታወስ ተተኪ ጀግኖች ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዣዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

ለኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ መታሰቢያ የተሰየመው የአደባባይ፣ በሀድያ አስተዳደርና ልማት ማህበር ድጋፍ የተገነቡት የመታሰቢያ ሐውልትና የሊች ጎጎ አዳሪ ትምህርት ቤት የምረቃ ሥነሥርዓት ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።

በሥነሥርዓቱ ላይ የታደሙት ሌተናል ጄኔራል ይልማ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ቅኝ ገዢዎችን አሳፍራ የመለሰች ታላቅ ታሪክ ያላት ሀገር ነች።

ጀግናው ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ በአየር ኃይል አብራሪነት እንዳሰለጠኗቸው ገልጸው፤ የሀገር ፍቅርና ለሙያቸው ታላቅ ክብር የነበራቸው የቁርጥ ቀን ልጅ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ኮሎኔል በዛብህ ከሌሎች የትግል ጓዶቻቸው ጋር በመሆን በሀገር የመጣ ጠላትን ለመመከትና አፀፋ ለመመለስ ቁርጠኛ አቋምና መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንደነበሩ በመግለጽ አድናቆታቸውን ተናግረዋል።

ጀግኖችን ማስታወስ የሀገር ክብርና ሕልውና አስጠብቆ ለማስቀጠልና ተተኪ ጀግኖችንን ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ የጀግኖችን ታሪክ በመዘከር ተተኪውን ትውልድ ታሪክ ተረካቢ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው ሐውልቱ ኢትዮጵያ የጀግኖች መፍለቂያ መሆኗን እንደሚያሳይና የትናንት ጀግኖችን እንደሚያስታውስ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ትናንት በነበሩ ጀግኖች መስዋዕትነት ተጠብቃ መቆየቷንና ዛሬም በልጆቿ ተከብራ  እንደምትቀጥል ማሳያ እንደሆነም አመልክተዋል።

በአሸባሪ ህወሓት የተገኘውም ድል አንድነትን በማጠናከር በልማት መስኮችም መድገም እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

የኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ወንድም የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው ወንድማቸው ለኢትዮጵያ ሕልውና መጠበቅ በከፈለው መስዋዕትነት ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።

የኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ  መታሰቢያ ሐውልት መሰራቱ ሌሎች መሰል ታጋዮችን ለማፍራት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ሕልውና እያስጠበቅን፤ ዕድገት ለማረጋገጥ መሥራት አለብን ብለዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ለጀግናው ኮሎኔል በዛብህ ሐውልት መሰራቱና አደባባይ በስማቸው መሰየሙ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም