ቀጥታ፡

"የኢትዮጵያ የጀግንነት ምንጭ ለሆኑ የሠራዊት አባላት እውቅና መስጠት የሀገር ኩራት ነው" -ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ሰቆጣ ጥር 22/2014... "አሸባሪው የህውሃት ቡድንን በመደመሰስ ጀብዱ የፈጸሙ የኢትዮጵያ የጀግንነት ምንጭ ለሆኑ የሠራዊት አባላት የሜዳልያ ሽልማት መስጠት የሀገር ኩራት ነው" ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የማዕከላዊ ዕዝ በተሰለፈባቸው አውደ ውጊያዎች የላቀ ድል ላስመዘገቡና ጀብዱ ለፈጸሙ የሠራዊት አባላትና አመራሮች ዛሬ የማዕረግ ዕድገት፣ ሽልማትና ዕውቅ ሰጥቷል።

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሥነስርዓቱ ላይ እንዳሉት  የሀገር መከላከያ ሠራዊት በህግ ማስከበርና በህብረ ብሄራዊ ዘመቻዎች የተሰጠውን ተልዕኮ በድል ተወጥቷል።

የአሸባሪው ህወሓት ሀገር የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ የመከላከያ ሠራዊት አስቸጋሪ መልክዓ ምድርና የአየር ፀባይ ሳይበግረው ትልቅ ተጋድሎ መፈፀሙን ገልፀዋል።

ከሰሜን ሸዋ ዞን ጀምሮ በተካሄዱ ተከታታይ ውጊያዎች የአሸባሪ ቡድኑን ሽንፈት ያከናነቡና ጀብድ የፈፀሙ የሠራዊት አባላትን ሜዳሊያ መሸለም የኢትዮጵያ ኩራት ነው ብለዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ እንዳሉት ይህም ካለፉት ዘመቻዎች ያገኙትን ልምድ በመጠቀም የአሸባሪ ቡድኑ እስኪደመሰስ ድረስ በሚካሄዱ ውጊያዎች በጠላት ላይ የተለመደውን ድል እንዲያስመዘግቡ መነሳሳት ይፈጥራል።

"የዛሬ የሜዳሊያ ተሸላሚ ጓዶች ያገኛችሁትን ሜዳሊያ የቤተሰብ፣ የጎረቤትና የሀገር ክብር በመሆኑ ወደ ቤተሰቦቻችሁ ላኩትና በክብር ያስቀምጡላችሁ" ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ይህ የሽልማት ሥነስርዓት ከሠራዊት ግንባታ ሂደት ጋር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን ከጦርነት አዙሪት ለማውጣት ለቀጣዩ ግዳጅ በየደረጃው ያሉ የሠራዊቱ አባላትና አመራሮች በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የሽብር ቡድኑን በግንባር የደረሰበትን ሽንፈት በቅጥረኞቹ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በሠራዊቱ ላይ የሚያካሂደውን ዘመቻ ከጦር ግንባር ድል ባልተናነሰ መልኩ ለመመከት ይሰራል ብለዋል።


የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌፍትናንት ጀነራል ዘውዱ በላይ እንዳሉት የዕዛቸው ሠራዊት በተሳተፈባቸው ግንባሮች አኩሪ ድል በማስመዝገብ ለኢትዮጵያ ኩራት ሆኗል።

በዚህም በአውደ ውጊያ ጀብድ ለፈፀሙ ምርጥ ተዋጊ፣ አዋጊና የውጊያ አገልግሎት ሰጭ የሠራዊት አባላትን ሚዳሊያና እውቅና መስጠት መቻሉ ለላቀ ግዳጅ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።


በመርሃ ግብሩ ላይም በአውደ ውጊያ ጀብድ የፈፀሙ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ የሜዳሊያ ሽልማትና የማዕረግ ዕድገት ማልበስ  ሥነስርዓት መካሄዱ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም