የአሸባሪውን ህወሓት ዳግም የጦርነት ትንኮሳ ኅብረተሰቡ በጀግንነት እየመከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአሸባሪውን ህወሓት ዳግም የጦርነት ትንኮሳ ኅብረተሰቡ በጀግንነት እየመከተ ነው
ሰመራ ጥር 22/2014 (ኢዜአ)... አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል በኪልበቲ-ረሱ ዞን እያደረገ ያለውን ዳግም የጦርነት ትንኮሳ ኅብረተሰቡ በጀግንነት እየመከተ መሆኑን የአፋር ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ቢላይ አህመድ ከአበአላ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ቀደም ሲል ሞክሮት ያልተሳካለትን የእብሪት ወረራ በሌላ አቅጣጫ ለማሳካት ዳግም የጦርነት ትንኮሳ እያደረገ ነው።
የሽብር ቡድኑ በኪልበቲ-ረሱ ዞን አበአላ ከተማ ላይ በከባድ መሣሪያ የታገዘ ጥቃት ሲፈጽም መቆየቱን ገልጸው፤ ከሳምንቱ መጀመሪያ ጀምሮ ከፍተኛ የሰው ኃይል በማሰለፍ በተለያዩ ወረዳዎች ላይ ግልፅ የጦርነት ትንኮሳ ከፍቷል ብለዋል።
ምክትል ኃላፊው እንዳሉት የሽብር ቡድኑ ዳግም የጦርነት ትንኮሳ እየፈጸመባቸው ካሉት ወረዳዎች መካከል አበአላ፣ መጋሌ፣ በራህሌና ኩነባ ይገኙበታል።
የሽብር ቡድኑ ዳግም የጦርነት ትንኮሳ የከፈተው ቀደም ሲል በተለያዩ ግንባሮች የሀገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ መስመር ለመቆጣጠር ያደረገው ያልተሳካ ሙከራ አካል መሆኑንም አቶ ቢላይ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የሀገሪቱን ገፅታ በማጠልሸት በሀገሪቱ የሰላምና ፀጥታ ችግር ያለ በማስመሰል የዓለም አቀፉን ማህረብሰብ ለማደናገር ከተለመደ ሴራው ያለፈ ዓላማ የለውም ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ ዕድሜውን ለማራዘም የትግራይ ታዳጊ ህጻናትን ከእናቶቻቸው ጉያ አስገድዶ በመንጠቅ ዳግም በጦርነት ማግዶ ሊያስፈጃቸው እንደሆነም አስረድተዋል።
እንደ አቶ ቢላይ ገለጻ የሽብር ቡድኑ ታዳጊ ህጻናትንና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ወጣቶችን በግፍ በጦርነት በመማገድ ለትግራይ ሕዝብ ምንም አይነት ርኅራሄ የሌለው መሆኑን አረጋግጧል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር በአፋር ንጹሃን አርብቶ አደሮች ላይ የጭካኔ ግድያ በመፈጸም ለአፋር ህዝብ ያለውን ስር የሰደደ ጥላቻ በተግባር ማስመስከሩንም ገልጸዋል።
ምክትል ኃላፊው እንዳሉት ከስህተቱ የማይማረው አሸባሪው ህወሓት ሰሞኑን በኪልበቲ-ረሱ የከፈተዉ ጥቃት ግብአተ-መሬቱን ከማፋጠን ባለፈ ትርጉም እንደማይኖረዉ አረጋግጠዋል።
የአፋር ህዝብ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የሸብር ቡድኑን በጀግንነት ፊት ለፊት ተጋፍጦ መቆሚያ መቀመጫ እያሳጣው እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የሽብር ቡድኑ በእብሪት ተወጥሮ በአፋርና በኢትዮጵያ ህዝብ ክብርና ሉዓላዊነት ላይ የቃጣውን ጥቃት በአስተማማኝ ሁኔታ እስኪቀለበስ ድረስ ሁሉም ዜጋ በአንድነት ቆሞ ጠላትን መመከት አለበት ብለዋል።
የዱብቲ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አብደላ ሙሳ በሰጠው አስተያየት የሽብር ቡድኑ ከዚህ በፊት አፋርን በጉልበት መያዝ እንደማይቻል በሚገባው ቋንቋ አነጋግረነዋል።
የሽብር ቡድኑ አሁንም ተስፋ ቆርጦ በኪበልቲ-ረሱ የጀመረው ዳግም የጦርነት ትንኮሳ አጥፍቶ የመጥፋት ተግባርን በጀግንነት በመፋለም የኢትየጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።
የሽብር ቡድኑ "እኔ ሀገር ካልመራሁ በሰላም አትኖሩም" በሚል እብሪት በተደጋጋሚ እየፈጸመ ያለውን የጦርነት ትንኮሳ አንድ ሆነን እናመክነዋለን ያሉት ደግሞ አቶ ኡመር መሀመድ ናቸው።
የአፋር ህዝብ ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን አስፈላጊውን መስዋዕትነት በመክፈል ሕልውናውን እንዳረጋገጠው ሁሉ አሁንም የሽብር ቡድኑን ዳግም እየፈጸመ ያለውን የጦርነት ትንኮሳ በአንድነት እንቀለብሰዋልን ብለዋል።
የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አሸባሪው ህወሓት በአፋር ላይ የዘር ማጥፋት (Genocide) ወንጀል እየፈፀመ መሆኑን አስታውቋል።
አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል በተለያዩ ወረዳዎች ጋሊኮማን ጨምሮ ያካሄደውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በኪልበቲ ረሱ ዞንም በመድገም በተለያዩ ወረዳዎች ህፃናት፣ ሴቶችና አዛውንቶችን በአሰቃቂ ሁኔታ እየገደለና እያቆሰለ መሆኑን በመግጫው አመልክቷል።