ቀጥታ፡

ውሳኔው አፍሪካውያን የትኛውንም ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበሉ በግልፅ አቋማቸውን ያሳዩበት ነው

ሚዛን ጥር 22/2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ መሪዎች 35ኛው የሕብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ያስተላለፉት ውሳኔ አፍሪካውያን የትኛውንም ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበሉ በግልፅ አቋማቸውን ያሳዩበት ነው ሲሉ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ምሁራን አስታወቁ።

በዩኒቨርሲቲው  የታሪክ ትምህርት  መምህር አጥናፉ ምትኩ እንዳሉት የአፍሪካ መሪዎች የአፍሪካ ሕብረት 35ኛ ጉባኤ በሕብረቱ መቀመጫ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ያስተላለፉት ውሳኔ በውስጥ ጉዳያቸው የማንንምጣልቃ ገብነት እንደማይቀበሉ በግልፅ አቋማቸውም ያመላከቱበት ነው።

አንዳንድ የምዕራባዊያን እና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው በኢትዮጵያ ሰላም እንደሌለ በማስመሰል ጉባኤውን በአዲስ አበባ እንዳያካሂዱ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር ያደረጉትን ከንቱ ጥረትም  ያመከነ ነው ብለዋል።

ለእነዚህን አካላት የሐሰት መረጃ  ጆሮ ሳይሰጡ ጉባኤው በሕብረቱ መቀመጫ በሆነችው በአዲስአበባ እንዲደረግ መወሰናቸው ትልቅ መልእክት የሚያስተላልፍ መሆኑን አውስተዋል።

ከዚህም ባሻገር የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ዳግም በማበብ ውጤት እያስመዘገበ እንዳለ ፍንጭ የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ በበቃ ዘመቻ የታየው አንድነትና ህብረት ይህን የሚመሰክር እንደሆነ ተናግረዋል።

ምዕራባውያን አፍሪካ ጠንካራና በራሷ መቆም እንዳትችል እየሰሩመሆናቸውን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ለእነሱ የማትንበረከክና ለአፍሪካውያን ነጻነት ጥብቅና የምትቆም ሀገር መሆኗ እንደላስደሰታቸው አስረድተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውኃ እንዳይሞላ ጫና በመፍጠርና ከአሸባሪው ህወሓት ጋር አብረው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያላቸውን ፍላጎት በግልፅ ማሳየታቸውንም ተናግረዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን መሻገሯና  ሰላም መሆኗ ያልተዋጠላቸው አካላት በሚዲያዎቻቸው ጭምር የሀሰት ዘገባዎችን በማሰራጨት ዜጎቻቸውን ውጡ እስከ ማለት መድረሳቸው ትዝብት ላይ እንደሚጥላቸው ጠቅሰዋል።

አፍሪካውያን መሪዎች ግን እውነትን እንጂ የእነርሱን ጉትጎታ ባለመቀበል ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ወስነው ፓን አፍሪካኒዝምን ዳግም በማፅናታቸው  ኮርተናል ብለዋል።

የአፍሪካ መሪዎች ውሳኔ የእጅአዙር ቅኝ ግዛት በቃ የሚል አንድምታ ያለው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርስቲው የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መምህር ሙሉቀን አየለ ናቸው።

ይህ ትልቅ ድል  ደግሞ ኢትዮጵያ ያከናወነችው ጠንካራና የማይበገር የዲፕሎማሲ ውጤት ማሳያ ነው  ሲሉ ተናግረዋል።

ሁሉን አድራጊና ወሳኝ ነን ባዮች አቋማቸውን እንዲፈትሹ የሚያደርግ ውሳኔ በመወሰን አፍሪካውያን ወንድሞች  ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን ያረጋገጡበት የታሪክ አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እንደ መምህር ሙሉቀን ገለፃ አፍሪካውያን ቁርጠኛና በራስ የማድረግ አቅም ያላቸው በሕብረት የሚያምኑ ወንድማማቾች መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ለአፍሪካ አንድነት ንቅናቄ ፓን አፍሪካኒዝምና የአፍሪካ ሕብረት ምስረታ አስተዋፅኦ ያላት ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን መሰብሰብ ያበረከተችው አስተዋጽኦ መቼም እንደማይዘነጋ አስምረውበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም