ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት መርሃ ግብር ነድፎ ወደ ትግበራ መግባቱን አስታወቀ

አዳማ፣   ጥር 21/2014/ኢዜአ/ ግብርና ሚኒስቴር ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት መርሃ ግብር ነድፎ ወደ ትግበራ መግባቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በልማት ፕሮግራሙ ዙሪያ ከሁሉም ክልሎች ከተውጣጡ የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ መክሯል።

ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ዋና ትኩረቱ ለውጭ ገበያ በሚቀርብ የአቮካዶ ምርት ላይ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን በምክክር መድረኩ ላይ ገልጸዋል።

ፕሮግራሙን ለማስጀመር ኢንሼቲቭ መቀረጹን ገልጸው፤ በተለይ ሀገራችን በቤተሰብ ደረጃ በምግብ ራሷን እንድትችልና የስነ ምግብ ስርዓትን እውን እንድታደርግ ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተለይ ኢንሼቲቩ አርሶ አደሮች፣ ባለሃብቶች፣ ድርጅቶችና ሰፋፊ የእርሻ መሬት ያላቸው ማህበራዊ ተቋማት ለውጭ ገበያ በሚቀርብ የአቮካዶ ልማት በስፋት እንዲሳተፉ ለማስቻል እንደሆነም ተናግረዋል።

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ ቡና፣ አበባና የቅባት እህሎች ቀጥሎ አቮካዶ ከምግብነት ባለፈ ከሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት በኋላ በአራተኛ ደረጃነት የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኝ ጭምር ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለፕሮግራሙ ውጤታማነት መንግሥት ምቹ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ኢንሼቲቮችን ቀርፆ ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።

ዩኒቨርቲሲዎች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት በተቀናጀ መልኩ በዘርፉ ልማትና ዕድገት ቀጣይነት ላይ መስራት አለባቸው ብለዋል።

ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም በዘጠኝ ክልሎች በ157 ወረዳዎችና 4ሺህ 710 ቀበሌዎች የሚካሄድ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በመድረኩ ላይ ፁሑፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር ዓሊ ሙሐመድ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አቮካዶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ልማቱ በ31 ሺህ ሄክታር ላይ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በአቮካዶ ልማት ፕሮግራም አሁን በ31 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ያለውን ልማት ከ104 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የማስፋት ግብ መቀመጡን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ምርቱ አውሮፓ፣ መካክለኛው ምስራቅና ደቡብ ምስራቅ እሲያ ሀገሮችን ጨምሮ ለ20 የዓለም ሀገሮች ገበያ ተደራሽ መሆኑን ፕሮፌሰር ዓሊ ገልፀዋል።

በዋናነት የልማት ፕሮግራሙ የተቀረፀው አቮካዶን በብዛትና በጥራት በማምረት ከምግብነት ባለፈ በዓለም ገበያ ውድድር ውስጥ  በስፋት ዘልቀን ለመግባት ነው ብለዋል።

ለዚህም ዘጠኙን ክልሎች ያማከለ 10 የአቮካዶ ልማት ክላስተር ከመደራጀቱም ባለፈ ምርቱን ወደ ውጭ ለመላክ የተቀላጠፈ የማጓጓዣ አገልግሎትና የማቀዝቀዣ መጋዘኖች በሞጆ ደረቅ ወደብ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም 10ሩን የአቮካዶ ልማት ክላስተሮችን ማእከል ያደረገ 380 የምርት መሰብሰቢያ መጋዘኖችና 10 የምርት ማደራጃዎች ለመገንባት መታቀዱንም አስታውቀዋል።

አሁን ያለውን 10 የአቮካዶ ችግኝ ማፍያ ጣቢያን ወደ 37 ለማሳደግ እየተሰራ ሲሆን፤ ከፍተኛ ምርት የሚሰጥና በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆነ የአቮካዶ ዝርያ ተለይቶ እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም