ቀጥታ፡

የይርጋለም ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ 51 የህክምና ዶክተሮችን ዛሬ አስመረቀ

ይርጋለም፣ ጥር 21/2014 (ኢዜአ.) የይርጋለም ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ ለ5ኛ ጊዜ 51 የህክምና ዶክተሮችን ዛሬ አስመርቌል።

በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር የጤና ስርአት እቅም ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ እንደገለፁት የጤና ባለሙያዎች ቀጣይነት ላለው የጤና ስርአት የጀርባ አጥንት ናቸው።

የጤና ተቋማትም ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመው በክፍለ ዘመኑ በጤናው ዘርፍ እየተፈጠሩ ካሉ መልካም ተሞክሮዎች በመማር ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ለመሻገር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ የጤና አገልግሎትና የዘርፉ ባለሙያዎችን የሥራ ሁኔታ ለማሻሻል እንዲቻል የጤና ፖሊሲ ክለሳና የአምስት ዓመት የጤና ዘርፍ የለውጥ እቅድ መንደፉን አመልክተዋል።

እንዲሁም የሀገሪቱ የጤና አገልግሎት የሚመራበትና የሚገዛበት የጤና አዋጅ ዝግጅትና የሰው ኃይል ልማት መሪ እቅድ ተቀርጾ በመተግበር ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በመካከለኛ ደረጃና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል የማገዝና ሌሎችም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።

የይርጋለም ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ ለሰልጣኞቹ ከሚሰጠው ሙያዊ እውቀትና ክህሎት ባሻገር የጤናው ዘርፍ ፍላጎትና የጤና አገልግሎት ስርዓትን የተረዱና የጥራት ማሻሻያ ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች በብቃት ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል።

የይርጋለም ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ ዲን ተወካይ ዶክተር ደሳለኝ ዳባሮ በበኩላቸው ኮሌጁ በ2004 ዓ.ም ከተቋቋመ ጀምሮ በተፈጥሮ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውን ሰልጣኞች ተቀብሎ በህክምና ሲያሰለጥን መቆየቱን ተናግረዋል።

ኮሌጁ እስካሁን 145 ሀኪሞችን ማስመረቁንና በዛሬው እለትም አራት ሴቶችን ጨምሮ 51 የህክምና ዶክተሮችን ማስመረቁን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም