የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በአፋር ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በአፋር ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ
ሰመራ፣ ጥር 21/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሙላት ገዛኽኝ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት በሽብር ቡድኑ ወረራ በአፋርና አማራ ክልሎች ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል።
ተቋሙ በሽብር ቡድኑ ወረራ የተፈናቀሉና የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍ ሂደት የሚጠበቅበትን ማህበራዊ ሃላፊነት ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው እለት በአፋር ክልል ለተፈናቀሉና ለተጎዱ ወገኖች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ተቋሙ በቀጣይ ክልሉን በመልሶ ማልማት ሂደት ለመደገፍ 3 ሚሊዮን ብር መመደቡን ሀላፊው አስታውቀዋል ።
ድጋፉን የተረከቡት የአፋር ክልል ፍይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊና የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አህመድ መሀመድ የሽብር ቡድኑ በክልሉ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።
ለተጎጂዎች ሰብአዊና እርዳታ ማቅረብም ሆነ መልሶ ማቋቋም በመንግስት አቅም ብቻ ሊሸፈን የሚችል ባለመሆኑ ተቋማትና ህዝቡ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል ።