ቀጥታ፡

የአዳማ ከተማዋ ፖሊስ መምሪያ ሰርጎ ገቦችን ለመቆጣጠር በትኩረት እየሰራ ነው

አዳማ፣ ጥር 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሀገር ገፅታን ለማጠልሸት የሚሯሯጡ የአሸባሪ ቡድኖች ተላላኪ ሰርጎ ገቦችን በመከላከልና በመቆጣጠር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ዳይሬክተር ኮማንደር መንግሥቱ ኢጃራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተላላኪዎቻቸውን አስርገው በማስገባት የአገር ግጽታን ለማበላሸት የሚያደርጉትን ሙከራ አላቋረጡም።

የአሸባሪ ቡድኖቹን ሙከራ ዕውን ለማድረግ ተልዕኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ ተላላኪዎችን ለማክሸፍ ፖሊስ በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።

አዳማ ከጂቡቲ አዲስ አበባ መስመር ላይ የሚትገኝ ማዕከል በመሆኗ በቀን ከ33 ሺህ በላይ እንግዶች ገብተው የሚወጡባት ከተማ መሆኗን ጠቅሰው፤

ከዚህ በፊት ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ ይደረግ የነበረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ፖሊስ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማወክ የጦር መሳሪያ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድኖቹን ተላላኪዎች ከነጦር መሳሪያቸው በቁጥጥር ስር አውሎ ለህግ ማቅረቡንም ገልጸዋል።

ፖሊስ ጥረቱን በማጠናከር አስተማማኝ ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ በትጋት እየሰራ ነው ያሉት ኮማንደር መንግስቱ፤ ከኃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመተባበር ሌት ተቀን እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በከተማዋ የሠላምና ፀጥታው ሥራው በ28 ቋሚ የፍተሻ ኬላዎችና ከ150 በላይ በሚሆኑ ተንቀሳቀሽ የፍተሻ ጣቢያዎች 24 ሰዓት ሙሉ እየሰሩ ነው።

ህብረተሰቡ በየደረጃው ካለው የፀጥታ ኃይል ጋር ተቀናጅቶ አካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ እያደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የአዳማ ከተማ ፀጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መኩሪያ ዲንቁ እንዳሉት፤ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ የሰላምና ፀጥታ  ስራ እየተሰራ ነው።

የአፍሪካ ሕብረት 35ኛ የመሪዎች ጉባኤ ሀገራዊ ገፅታ በመገንባት ሂደት የጎላ ሚና አለው ያሉት ኃላፊው፤ ጉዳዩ ከአዲስ አበባ ባለፈ እኛንም በቀጥታ የሚመለከት ነው ብለዋል።

በተለይ በምስራቅ ሸዋ ዞን የፀረ ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴ ከመቆጣጠርና ሰርጎ ገቦችን ለመያዝ ከቤት ለቤት ፍተሻ ጀምሮ በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም