ቀጥታ፡

ጤና ሚኒስቴር ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒት ድጋፍ አደረገ

ደሴ፣  ጥር 21/2014(ኢዜአ) ጤና ሚኒስቴር ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሃት ወራሪ ሀይል ለወደሙ ጤና ተቋማት ስራ ማስጀመሪያ ከ21 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒት ድጋፍ አደረገ።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት ዘላለም በድጋፍ ርክክቡ ላይ እንደገለፁት በሽብር ቡድኑ የወደሙ ጤና ተቋማትን በጋራ መልሶ ማቋቋምና ለህዝብ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል።

"ሚኒስቴሩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበርና ተቋማትን እርሰ በእርስ በማስተሳሰር በሚደረግ ድጋፍ ውድመት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት ተስተካክለው አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረገ ነው" ብለዋል።

በዛሬው እለት ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒቶች ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ድጋፉ የተለያዩ የህክምና ማሽኖች፣ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችና መድሃኒቶችን ያካተተ መሆኑን አመልክተዋል።

በህክምና እጦትና መድሃኒት እጥረት የሚሞቱ ዜጎችን በጋራ ለመታደግ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አብዱል ከሪም መንግስቱ በበኩላቸው በአሸባሪው ህወሃት 2 ሺህ 343 ሆስፒታሎች ፣ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች በተለያየ ደረጃ ዘረፋና ውድመት ደርሶባቸዋል።

ጉዳት ለደረሰባቸው ጤና ተቋማት በቀላሉ የሚስተካከለውን እየተስተካለ ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ዛሬ የተደረገው ድጋፍም መልሶ የማቋቋም ስራውን እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።

በአማራና በአፋር ክልሎች የወደሙ የጤና ተቋማትን ለማቋቋም እስከሁን ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን የገለፁት ደግሞ በድጋፉ የተባበሩት የኢትዮጵያ ቤተሰብ መመሪያ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ሀብቴ ናቸው።

በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት ዛሬ በተደረገው ድጋፍ ማህበሩ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የህክምና ቁሳቁስ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በድጋፍ ርክክቡ የፌደራልና የክልል አመራሮች እንዲሁም የዘርፉ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን አመራሮቹና ባለሙያዎቹ በደሴ ከተማ በሽብር በድኑ ውድመት የደረሰባቸው የጤና ተቋማትን ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም