አገልግሎቱ ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ በ19 ከተሞች ዘመናዊ ህንጻዎች ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አገልግሎቱ ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ በ19 ከተሞች ዘመናዊ ህንጻዎች ሊገነባ ነው
ጎንደር ፣ ጥር 21/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ በአገሪቱ በ19 ከተሞች ዘመናዊ ሕንጻዎች እንደሚገነባ አስታወቀ፡፡
አገልግሎቱ በ380 ሚሊዮን ብር ወጭ በጎንደር ከተማ ለሚያስገነባው ባለ 10 ወለል ሕንጻ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት በዚህ አመት ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ በሀገሪቱ በ19 ከተሞች ዘመናዊ ህንጻዎች ይገነባሉ።
አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ በተለያዩ ከተሞች የሚገነቡት ህንጻዎች ተቋሙ ለጀመረው ያልተማከለ አደረጃጃትና የለውጥ ስራዎች አጋዥ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመላ አገሪቱ ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ለመጣው የኤሌክትሪክ ደንበኛ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የሕንጻዎቹ መገንባት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
የሕንጻ ግንባታዎቹ ለደንበኞችና ለሠራተኞች ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ለከተሞች እድገትና ውበት የራሳቸውን አስተዋጾ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ደረጃ በጎንደር፣ በደሴ፣ ደብረ ብርሃንና ደብረ ማርቆስ ከተሞች የሕንጻ ግንባታ የሚካሄድባቸው መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።
በጎንደር ከተማ በ380 ሚሊዮን ብር ወጪ ለሚገነባው ባለ 10 ወለል ሕንጻ ከተማ አስተዳዳሩ 6 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ መስጠቱን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ጣሰው ናቸው።
ሕንጻው በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ጠቁመው ህንጻው ለደንበኞች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ ክፍሎች እንደሚኖሩት አመላክተዋል።
የሕንጻው መገንባት ለከተማው ገጽታ ጉልህ ድርሻ እንዳለውና ለበርካታ ወገኖች የሥራ እድል እንደሚፈጥር የገለጹት ደግሞ የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጎንደር ከተማን የኤሌትሪክ አቅርቦት ችግር ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ጠቁመው ጅምሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለሕንጻው ግንባታ ሥራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል ።