አሸባሪው ህወሓት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሷል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሷል
ጎንደር፣ ጥር 21/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ በፈፀመው ዘረፋና ውድመት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሱን የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የስድስት ወራት የዕቅድ ክንውን አፈጻጸሙን በጎንደር ከተማ ገምግሟል።
በመድረኩም የ11 ሪጅኖች እና የ28 ዲስትሪክት የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የአማራ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰለሞን ጣሰው እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ጉዳት ያደረሰው በክልሉ ሰባት ዞኖችና በበርካታ የከተማ አስተዳደሮች ነው።
የጥፋት ቡድኑ በኤሌክትሪክ ተሸካሚ መስመሮችና ምሰሶች፣ በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና በአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ላይ ባደረሰው ዝርፊያና ውድመት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ጉዳት አድርሷል ብለዋል።
በወረራው ህወሓት ምክንያት በክልሉ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ይገኝ የነበረ 390 ሚሊዮን ብር ገቢም መታጣቱን አቶ ሰለሞን ገልፀዋል።
የሽብር ቡድኑ በመሰረተ ልማቶቹ ላይ ያደረሰውን ውድመትና ጉዳት መልሶ በመጠገን ደንበኞች አቅም በፈቀደ መጠን አገልግሎቱን እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል።
በህልውና ዘመቻው ከሽብር በድኑ ነፃ በወጡ የክልሉ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን መልሶ ለማስጀመር በተደረገ ጥረት አገልግሎቱ 370 ሚሊዮን ብር ወጭ ማድረጉንም አመልክተዋል።
የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፋፃሚ አቶ ያሲን አሊ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በክልሉ ወረራ በፈጸመባቸው ጊዜያት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ 130 ሚሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት አድርሷል።
"ጉዳት የደረሰባቸውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ጠግኖ መልሶ ወደ አገልግሎት ለማስገባት በተደረገ ጥረት በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ አገልግሎቱን ዳግም ማስጀመር ተችሏል" ብለዋል።
በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰባቸውን መሰረተ ልማቶች መልሶ ሥራ ከማስጀመር ጎን ለጎን የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ መሰራቱን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ናቸው።
አቶ ሽፈራው እንዳሉት ተቋሙ በግማሽ ዓመቱ በ81 አዲስ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ 176 ሺህ አዲስ ደንበኞችን አገልግሎቱን እንዲያገኙ ተደርጓል።
በቀሪ ወራትም በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ጥገና በማጠናከር ደንበኞች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከ4 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል።