በሊበን ዝቋላ ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የስምንት ሰዎች ህይወት አለፈ

76
አዳማ ነሀሴ 24/2010 በምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ዝቋላ ወረዳ  ትናንት ምሽት በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ አደጋው የደረሰው ከአዲስ አበባ ወደ ሻሸመኔ 18 ሰዎችን አሰፍሮ ይጓዝ የነበረው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 51865 ሀይሩፍ የህዝብ ማመላለሻ አሸዋ ጭኖ ከመቂ ወደ አዲስ አበባ ከሚያመራ  ሲኖ ትራክ ጋር በመጋጨቱ ነው፡፡ በሊበን ዝቋላ ወረዳ ቦጌቲ ቦሮ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ምሽት ሶሰት ሰዓት አካባቢ  በደረሰው በዚሁ አደጋ በህዝብ ማመላለሻው ውስጥ  የነበሩ የስምንት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ማለፉን የዞኑ ፖሊስ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡ በዘጠኝ ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ እና በአንድ ሰው ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በሳማ ሰነበት ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው፡፡ የሟቾቹ  አስክሬን ቤተሰቦቻቸው እንዲረከቡ መደረጉን ከማንደር አስቻለው ጠቁመው የሁለቱም አሽከርካሪዎች ለጊዜ ከአካባቢው በመሰወራቸው  ፖሊስ በቁጥጥር ስር ለማዋል  ክትትል  እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ የአደጋው መንስኤ በሌሊት ከማሸከርከር ጋር ተያይዞ የተከሰተ በመሆኑ አሸከርካሪዎች ህግና ደንብን ተከትለው ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ አሳስበዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም