የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሪፎርሞችን እየተገበረ ነው

189

ሀዋሳ፣ ጥር 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሀገሪቱ ግዙፍ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሪፎርሞችን እየተተገበረ መሆኑን አስታወቀ።

የሚኒስቴሩና የክልሎች የ2014 በጀት ዓመት የዘርፉ የስድስት ወራት ዕቅድ ክንውን አፈፃፀም ግምገማና የምክክር መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር በከር ሻሌ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ የመጣው ለውጥና ሪፎርም ከወለዳቸው ተቋማት መካከል አንዱ ነው።

ተቋሙ በተለያዩ ተቋማት ተበታትነው የሚፈጸሙና ፋይዳቸው ተመጋጋቢ የሆኑትን ስራዎች በማሰባሰብ ወጥነት ባለውና በአንድ በሚመራበት መልኩ መደራጀቱን ገልጸዋል።

አደረጃጀቱን ተከትሎ ሥራንና ሰራተኛን፣ ክህሎትንና ሙያን እንዲሁም የስራ እድልና የስራ ገበያ ስምሪትን ያማከሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውን ተግባራት ማከናወኑን  አስታውቀዋል።

ከቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ጥረት መደረጉን ያስታወቁት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በባለሙያውና አመራሩ ርብርብ ቀጣይ አቅጣጫዎችና ቁልፍ የሪፎርም ሀሳቦችን መለየታቸውንና የ10 ዓመት ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫዎች መነደፉን ገልጸዋል።

በሚኒስቴሩ የስራ ስምሪትና ስራ ገበያ መረጃ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደጀኔ በቀለ በበኩላቸው በእያንዳንዱ ሴክተር ለዜጎች ሥራ ለመፍጠር እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ  ገልጸዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት 31 ሺህ ዜጎች የውጭ የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም