ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልከው የማር ምርት መጠን እየቀነሰ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ነሀሴ 24/2010 ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልከው የማር ምርት በጥራት ጉድለት ሳቢያ መጠኑ በየጊዜው ቅናሽ እያሳየ መሆኑ ተገለፀ። በዘርፉ የሚታየውን የጥራት ችግር ለመፍታትም የጥራት ቁጥጥር የሚሰጡ ተቋማትን አቅም የሚያሳድግ ፕሮጀክት በዘርፉ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን ብሄራዊ የጥራት መሰረተ ልማት ፕሮጀክት በዘርፉ ጥራት ለማምጣት ከኢትዮጵያ ማርና ሰም አምራችና ላኪዎች ማህበር እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መክሯል። በዚሁ ወቅት እንደተገለፀው አገሪቱ እ.አ.አ ከ2013 ጀምሮ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የማር ምርት መጠን እየቀነሰ መጥቷል። የኢትዮጵያ ማርና ሰም አምራችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ውብሸት አዱኛ ኢትዮጵያ የማር ምርትን ወደ አውሮፓ መላክ የጀመረችው ከ10 አመት በፊት ነበር። አገሪቱ እ.አ.አ በ2013 ከ880 ቶን በላይ የማር ምርት ለውጭ ገበያ ብታቀርብም ወደ ውጭ የምትልከው ምርት እየቀነሰ መጥቶ ባለፈው ዓመት የተላከው የማር ምርት ወደ 500 ቶን ሊወርድ ችሏል። የተላከው የማር ምርት መጠን የቀነሰው በጥራት ጉድለት መሆኑን ጠቅሰው የማር ምርታማነትንና ጥራትን ለማሳደግ የዘርፉን ችግሮች መፍታት እንደሚገባም ይናገራሉ። በሌሎች ማር አምራች አገራት ከአንድ ቀፎ ከ50 እስከ 80 ኪሎ ግራም ማር የሚገኝ ሲሆን በኢትዮጵያ ግን ዘመናዊ ከሆነው ቀፎ እስከ 25 ኪሎ ግራም ነው የሚገኘው። ለምርታማነትና ጥራት ችግር ምክንያት የሚሆኑት የግብዓት አቅርቦት ችግር፣ የዘርፉ በቴክኖሎጂና አዳዲስ አሰራሮች አለመደገፍ እንዲሁም ዘርፉን የሚያሰራ የህግ ማዕቀፍ አለመኖር እንደሆነም ተናግረዋል። ንብ አናቢዎች ያላቸውን እውቀት ማሳደግና በግብዓትና በቴክኖሎጂዎች መደገፍ  እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ምርቱን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ተረክበው ጥራቱን አጓድለው ለገበያ የሚያቀርቡ ሰዎችም በማር ጥራት ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ለማስቀረት የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንደሚገባም ገልፀዋል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበኩሉ በጥራት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ብሄራዊ የጥራት መሰረተ ልማት ፕሮጀክት መዘጋጀቱን ገልጿል። የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን ፍስሃ እንዳሉት ሚኒስቴሩ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በጥራት ላይ በተደረገ ጥናት መሰረት ፕሮጀክቱ ተቀርጿል። ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የሚደገፈው ይህ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት በእርሻ ምርቶች፣ ጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ዘርፍ ላይ የሚታዩ የጥራት ችግሮችን ለማሻሻል የተዘጋጀ ነው። ፕሮጀክቱ የማር ምርትን ጥራት ለማሳደግም የሚሰራ ሲሆን ይህን ለማድረግም የጥራት ቁጥጥር አገልግሎት በሚሰጡት ተቋማት አቅም ማነስ ምርቱ አለም አቀፍ ተቀባይነት እያጣ በመሆኑ እነዚህን ተቋማት ከስልጠና ጀምሮ የመሳሪያ ድጋፍ በማድረግ የማጠናከር ተግባርም ያከናውናል ብለዋል። ተቋማቱን በማጠናከር አለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖራቸውና ያለባቸውን የአገልግሎት ወሰን እንዲያሰፉ እንደሚደረግም ነው የገለፁት። ከዚህም በተጨማሪ ፕሮጀክቱ ከአምስት አመት በኋላም ሲጠናቀቅ ስራውን በባለቤትነት የሚመራ የጥራት መሰረተ ልማት ዳይሬክተር በሚኒስትሩ መቋቋሙን ገልፀው ፕሮጀክቱ የዚህን ዳይሬክቶሬት አቅም ለማሳደግም ይሰራል ነው ያሉት። የምርቱን ጥራት ለማረጋገጥ አገልግሎት ሰጪውን ማብቃት አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ ወንድወሰን ለዚህም የግሉን ዘርፍ የመደገፍ ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ እ.አ.አ በ2022 የሚጠናቀቅ ሲሆን ከዓለም ባንክ በተገኘ የ50 ሚሊዮን ብድር የሚከናወን ነው። በኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የማር ምርት የሚገኘው በባህላዊ መንገድ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው ለጠጅ ዝግጅት እንደሚውልም በመድረኩ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም