በአማራ ክልል ከቀያቸው ተፈናቅለው ከነበሩ ዜጎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑትን ወደ አካባቢያቸው መመለስ ተችሏል

30

ጥር 20/2014(ኢዜአ) በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው ከነበሩ ዜጎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑትን ወደ አካባቢያቸው መመለስ መቻሉን የክልሉ የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታወቀ።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዘላለም ልጅዓለም አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአማራ ክልል ፈጽሞት በነበረው ወረራ ምክንያት ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው መቆየታቸውን ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡

ከእነዚህም ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑትን ወደ ቀያቸው መመለስ መቻሉን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በቀያቸው ሆነው ድጋፍ  እየተደረገላቸው ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በሽብር ቡድኑ ወረራ ከቀያቸው ተፈናቅለው ከነበሩ ዜጎች በተጨማሪ ቡድኑ በፈጸመው ውድመትና ዝርፊያ ምክንያት ተጨማሪ ከ9 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም አሁን ላይ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን መደገፍና የመልሶ ማቋቋም ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በክልሉ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ለማድረግ በየወሩ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ እህል እንደሚያስፈልግም ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት፡፡

በመሆኑም መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ፣ ኀብረተሰቡና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን በመደገፍ ረገድ የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአጠቃላይ በክልሉ አሸባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማወቅ እየተከናወነ ያለው ዝርዝር ጥናት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ ጥናቱን መሰረት በማድረግ ለመልሶ ማቋቋምና ድጋፍ የሚሆን ስትራቴጂ እንደሚነደፍና ለዚሁ ስራ የሚውል ተቋማዊ አሰራር እንደሚዘረጋም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም