ሽብርተኛው ህወሃት ለሚያደርገው ትንኮሳ የመከላከያ ሰራዊትና የክልል ጸጥታ ሃይሎች እርምጃ የሚወስዱበት አቅጣጫ ተቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
ሽብርተኛው ህወሃት ለሚያደርገው ትንኮሳ የመከላከያ ሰራዊትና የክልል ጸጥታ ሃይሎች እርምጃ የሚወስዱበት አቅጣጫ ተቀመጠ

ጥር 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሽብርተኛው የህወሃት ቡድን ለሚያደርገው ትንኮሳ የመከላከያ ሰራዊትና የክልል ጸጥታ ሃይሎች በጥናት ላይ ተመስርተው እርምጃ የሚወስዱበት አቅጣጫ ተቀመጠ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተመራው የፌዴራል ጸጥታ ምክር ቤትና የክልል ርእሳነ መስተዳደሮች ውይይት በሀገራዊ ጸጥታ ሁኔታ ላይ የቀጣይ አቅጣጫ ላይ ትኩረት አድርጓል።
በምክክሩም ሀገሪቱ አሁን ያለችበት አንጻራዊ ሰላምና ጸጥታን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ማስቆምና በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠሩ ኢመደበኛ አደረጃጀቶችን ቅርጽ ማስያዝ እንደሚገባ ከስምምነት ተደርሷል።
በተለይ ሽብርተኛው የህወሃት ቡድን የሚያደርገውን ትንኮሳን ተከትሎ እርምጃዎች የሚወሰድበት አግባብ አቅጣጫ ተቀምጦለታል።
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በሀገሪቱ ቀጣይ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች ከወዲሁ መስመር የማስያዝና የማስተካካያ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አንስተዋል።
ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር፣ የኮንትሮባንድና መሰል እንቅስቃሴዎች የተገመገሙ ሲሆን፥ በውስጥ ያሉ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ቀጠናው ላይ ሰላምን ማስጠበቅ እና ሀገራዊ ግንኙነትን ማጠናከር ላይ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል ብለዋል።
የአገር መከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው የአሸባሪ ቡድኖችን እንቅስቃሴ በመገምግም እርምጃ መውሰድ የሚቻልበት ሁኔታን ከመመልከት ባለፈ አሸባሪዎች ላይ እርምጃ መውሰድን የተመለከተ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት።
የተቀመጡ አቅጣጫዎችም ሆነ የተደረሰባቸው ስምምነቶችን የፌዴራልም ሆነ የክልል የጸጥታ አካላትና አስተዳደሮች በየደረጃው ተግባራዊ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል ሲል የኤፍቢሲ ዘገባ አመልክቷል።