የህብረቱ ጉባኤ የአፍሪካውያን አንድነትና ወንድማማችነት ጠንካራ መሆኑን ዳግም ያረጋገጠ ነው- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የህብረቱ ጉባኤ የአፍሪካውያን አንድነትና ወንድማማችነት ጠንካራ መሆኑን ዳግም ያረጋገጠ ነው- ምሁራን
ጎንደር ጥር 20/2014 -(ኢዜአ)- ዘንድሮ የሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ የአፍሪካዊያን አንድነትና ወንድማማችነት ጠንካራ መሆኑን ዳግም ያረጋገጠ ነው ሲሉ የጎንደርና የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የህግና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን አስታወቁ፡፡
የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰናቸው ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸውን በተግባር ያረጋገጡበት ነው ሲሉም ምሁራኑ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ፍልስፍና መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አስተምሬ ለኢዜአ እንደገለጹት 35ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ የአፍሪካውያን አንድነትና ወንድማማችነት ጠንካራ መሆኑን ዳግም ያረጋገጠ ነው፡፡
“የህብረቱ ስብሰባ ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ለአለም ማህበረሰብ ግልጽ በሆነ መንገድ ታላቅ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው “ብለዋል፡፡
ጉባኤው ኢትዮጵያ ያለችበትን የሰላም ደረጃ አስተማማኝነት የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ክስተት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚለውን የአንዳንድ ምእራባዊያን መገናኛ ብዙሀን የሀሰት ዘገባ ያከሸፈ ከመሆኑም በላይ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያና ከእውነት ጎን መቆማቸውን ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው” ብለዋል፡፡
ጉባኤው የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፋቸውን ተደጋጋሚ ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔዎች ዳግም እንዲመረምር የሚያስገድድ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አመልክተዋል።
“ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በኖ ሞር ዘመቻ ያካሄዱት ሰፊ ንቅናቄና ሀገራችን ሰላም መሆኑዋን በማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ማክሸፍ ተችሏል” ያሉት ደግሞ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር አቶ መኳንንት ዱቤ ናቸው፡፡
“ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነትና የሊግ ኦፍ ኔሽን ግንባር ቀደም መስራች ሀገር እንደመሆንዋ አፍሪካውያን ለኢትዮጵያ ክብርና ታላቅነት የሰጡት ቦታ ታሪካዊነቱን የጎላ ያደርገዋል” ብለዋል፡፡
“የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ህብረቱ መወሰኑ ለሀገራችን መንግስትና ህዝብ ያለውን ክብርና አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን በህብረትና በአንድነት ለመቆማቸው ማረጋገጫ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በህብረቱ ስብሰባ የሚታደሙ የሀገር መሪዎችና ጋዜጠኞችን ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኙ ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማስጎብኘት ኢትዮጵያ ሰላም መሆኑዋን እንዲያረጋግጡ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በክብር የመቀበልና የማስተናገድ እሴቶቹን በመጠቀም አፍሪካውያን መሪዎቹን ከዚህ ቀደሙ በበለጠ በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ሊቀበል እንደሚገባ አቶ መኳንንት አስገንዝበዋል ።