የተሳፈሩበት ጀልባ ሞተር በመበላሸቱ ባህር ላይ ተይዘው የነበሩ 63 ኢትዮጵያውያን ህይወት ተረፈ - ኢዜአ አማርኛ
የተሳፈሩበት ጀልባ ሞተር በመበላሸቱ ባህር ላይ ተይዘው የነበሩ 63 ኢትዮጵያውያን ህይወት ተረፈ
አዲስ አበባ ነሀሴ 24/2010 የተሳፈሩበት ጀልባ ሞተር በመበላሸቱ ባህር ላይ ተይዘው የነበሩ 63 ኢትዮጵያውያንን ህይወት መታደግ መቻሉን ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት አስታወቀ። ኢትዮጵያዊያኑ ፍልሰተኞች ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ከጅቡቲ ተነስተው በየመን በኩል ሳዑዲ ዓረቢያ ለመግባት በሚጓዙበት ወቅት ነበር አደጋው የገጠማቸው። የሚታደጋቸው አጥተው ለስድስት ቀናት ባህር ላይ ከቆዩት ከእነዚህ ፍልሰተኞች መካከል ሁለቱ በውሃ ጥምና ምግብ እጦት ህይወታቸው አልፏል። ፍልሰተኞቹን መታደግ የተቻለው አንድ የንግድ መርከብ ካገኛቸው በኋላ ሲሆን መርከበኛውም ከሶማሊላንድ የበርበራ ክልል መንግስትና የሶማሊላንድ ባህር በር ጠባቂዎች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያዊያኑን አትርፈዋል። የህክምና፣ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የስነ-ልቦና ምክርና የመጠለያ አገልግሎት ከተሰጣቸው በኋላም ከሶማሊላንድ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። የፍልሰተኞቹ ዝቅተኛ እድሜ 15 ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 48 ዓመት ነው ተብሏል። በሃርጌሳ የኢትዮጵያ ቆንስላም ተመሳሳይ ድጋፍና የምክር አገልግሎት አግኝተዋል። ወደ አገራቸው ከገቡም በኋላ ራሳቸውን በሚያስችል ስራ ላይ እንዲሰማሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ በድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ ፕሮግራም አስተባባሪ ጁሊያ ሃርትሌብ አስታውቀዋል።