ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት በአማራ ክልል የመኖሪያ ቤታቸውን ላወደመባቸው ከ1 ሺህ 500 በላይ ዜጎች የመልሶ ግንባታ ስራ ተጀመረ

አዲስ አበባ ጥር 20/05/2014 (ኢዜአ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሸባሪው ህወሃት በአማራ ክልል በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች የመኖሪያ ቤታቸውን ላወደመባቸው ከ1 ሺህ 500 በላይ ዜጎች የመልሶ ግንባታ ስራ አስጀመረ።

የመልሶ ግንባታ መርሃ ግብሩ የተጀመረው በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ ሲሆን ለመንግስት ተቋማትና በችግር ላይ ለሚገኙ ወገኖችም ድጋፍ ተደርጓል።

በድጋፉ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የቢሮ እቃዎች እንዲሁም ምግብና አልባሳት  ልገሳ ተደርጓል።  

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ ባስተላለፉት መልእክት በሽብር ቡድኑ ችግር የገጠማቸውን በመደገፍ፣ የፈረሰባቸውን ቤት በመጠገንና መልሶ በመገንባት አለኝታነታችንን በተግባር ማሳየት አለብን ብለዋል።

በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል የመኖሪያ ቤቶቻቸው ለወደመባቸው ወገኖች፣ ለዘማች ቤተሰቦችና ጧሪ ለሌላቸው ወገኖች ሁላችንም ማገዝ አለብን ብለዋል።

በአማራና አፋር ክልሎች ችግር ለገጠማቸው ዜጎች ሚኒስቴሩ በወጣቶችና ሴቶች ንቅናቄ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተለይም ሴቶችና ህፃናትን እንዲሁም ጉዳት የገጠማቸውን ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች የስነ ልቦና ድጋፍ የማድረግ እቅድ መኖሩን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ በጦርነቱ ምክንያት የመኖሪያ ቤት ውድመት ለደረሰባቸው ከ1 ሺህ 500 በላይ ዜጎች መልሶ የመገንባት እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ደረስ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአሸባሪው ህወሃት ቤት ንብረት የወደመባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም