ቀጥታ፡

ኢትዮጰያን ጠላት የማይደፍራት ሀገር እንድትሆን የበኩላችንን እንወጣለን ---ዘማቾች

መተማ፤ ጥር 20/2014 (ኢዜአ)፡ በተገኘው ድል ሳይዘናጉ ኢትዮጰያን ጠላት የማይደፍራት ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ በምዕራብ ጎንደር ዞን ዘማች የሚሊሻ አባላት አስታወቁ።

በተለያዩ ግንባሮች ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከልዩ ሃይል አባላት ጋር ተሰልፈው ጀብድ ለፈፀሙ የሚሊሻ አባላት የምስጋና እና ዕውቅና መርሃ ግብር ትናንት  በገንዳ ውኃ ከተማ ተካሂዷል።

የሚሊሻ አበላቱ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት ላይ በተገኘው ድል ሳይዘናጉ  ጠላት የማይደፍራት ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚጠበቅባቸውን ሁሉ በሀገር ፍቅር ስሜት ይወጣሉ።

ዕውቅና ከተሰጣቸው መካከል አቶ መኮንን መኩሪያው ለኢዜአ እንደገለጹት ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከፀጥታ አካላትና ከሀገር ወዳድ ከሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመቀናጀት የህልውና ዘመቻውን በብቃት መመከት መቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይም አንድነታቸውን በማጠናከር የሽብር ቡድኑንም ሆነ ለሀገር ስጋት የሆነ ጠላትን በመመከት ሀገር እንዳትደፈር የድርሻቸውን  ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

አቶ ጥላሁን ተፈሪ በበኩላቸው ሚሊሻው ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ በአሸባሪው ህወሓት ላይ  ኪሳራ በማድረስ ሀገር ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይም እንደቀደሙት ጀግኖች አባቶች ታሪክ በማስቀጠል በጣላት የማትደፈር ሀገር እንድትሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓት ዳግም ወረራ ለማካሄድ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሽብር ቡድኑን ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከልዩ ሃይል ጎን በመሰለፍ ለመፋለም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በአሸባሪው ህወሓት ላይ በተገኘው ድል መዘናጋት ሳይኖር በቀጣይ በተሻለ መልኩ ተደራጅተው  በተጠንቀቅ መጠበቅ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ አቶ የሽወንድም ዋሲሁን ናቸው።

አሁን ላይ ለሀገርና ለህዝብ ሲባል ለተከፈለው መስዋትነት እውቅና መሰጠቱ ለቀጣይ ግዳጅ እንደሚያነሳሳቸው ተናግረዋል።

ብልፅግና ፓርቲ የዞኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢክስ ወርቄ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት የፈጸመውን ወረራ ለመመከት ሚሊሻው ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን ታላቅ ጀብዱ ፈጽሟል።

የሚኒሻው ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከልዩ ሃይሉ ጋር በመቀናጀት ባካሄደው ትግል ሀገርን ከመፍረስ መታደጉን ተናግረዋል።

ለሀገራቸው ክብር በአውደ ግንባር በጀግንነት በመፋለም የህይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ የጀግና ቤተሰቦችም መንግሥት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

በቀጣይ በተደራጀ አግባብ የሽልማትና የእውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብር እንደሚኖር  ኃላፊው ጠቁመው የተሰጠው እውቅናም መንግስት  ለጀግኖች ያለውን አክብሮት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም