ቀጥታ፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢኮኖሚውን ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ከግል ዘርፍ ማሕበራት ጋር ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19/2014(ኢዜአ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢኮኖሚውን ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ከግል ዘርፍ ማሕበራት ጋር ዛሬ ተፈራርሟል።


ስምምነቱ የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት መደገፍ የሚያስችል ትብብር ለመፍጠር ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።

ስምምነቱ በዘርፉ እውቅና ከተሰጣቸው የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም፣ ፈጣን የመልዕክት አገልግሎት ሰጪዎች ማሕበር እና የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበራት ጋር የተደረገ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታዋ ሁሪያ አሊ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማጎልበት እና የትብብር መድረኮችን በመፍጠር፣ በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ማጠናከር የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ያስችላል።

በዚህ ላይ የሚሰሩ ማህበራትም የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት እና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የስራ እድል ፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች በማበረታታት በዲጂታል ኢኮኖሚው ክህሎታቸውን ይበልጥ እንዲያዳብሩ እና ለሀገር ጥቅም እንዲያውሉ ለማስቻል እንደሚረዳም ተናግረዋል።

ስምምነቱ ለወጣቶች የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ከማድረጉም ባሻገር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማግኘትም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

ይህም ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት (ጂዲፒ) እና ለሀገሪቱ ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አክለዋል።

ስምምነቱን ከፈረሙት ማህበራት መካከል የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማህበር ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ባህሩ ዘይኑ፤ ስምምነቱ መንግስት በ2025 ዓ.ም ያቀደውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለመተግበር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማጠናከር የተቀመጡ እቅዶችና አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችን በፖሊሲ፣ በትግበራ እና በአቅም ግንባታ ለመደገፍ ያስችላል ነው ያሉት።

በዲጂታል ኢኮኖሚው ወጣቶች የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚያስችል አሰራር እንደሆነም ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን 2025 ስትራቴጂ ቀርጻ ወደ ትግበራ መግባቷ የሚታወስ ነው።

በዚህ ስትራቴጂም የኢንተርኔት ግንኙነት፣ ዲጂታል አገልግሎት እንዲሁም ፖሊሲና ስትራቴጂ ቅድሚያ የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም