የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል
ጥር 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አብዲሰይድ ሙሴ አሊ ተናገሩ።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አብዲሰይድ ሙሴ አሊን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሚኒስትሮቹ የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር ዙሪያና በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች እየተሳተፉ ላሉበት በሶማሊያ የአፍሪካ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ትብብርን ስለማጠናከርም ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
አቶ ደመቀ በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ ስላሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ለሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችንም ገልጸውላቸዋል።
መንግሥት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ እንዳይገባ ባለበት ፀንቶ እንዲቆይ መወሰኑን፣ በእስር ለይ የነበሩ ፖለቲከኞች መለቀቃቸውን፣ አካታች ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ማቀዱንም አብራርተዋል።
መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርሱ ቁርጠኛ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሆኖም አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል አብኣላ የጀመረው አዲስ ጥቃት የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እንቅፋት በመፍጠር የትግራይን ህዝብ ለአደጋ ዳርጎታል ብለዋል።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲሰይድ ሙሴ አሊ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን እያደረገችው ስላለው ጥረት አቶ ደመቀ ለሰጧቸው ማብራሪያ አመስግነዋል።
የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰሩም መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።