ቀጥታ፡

አለመግባባቶችና የተሳሳቱ ትርክቶች ምላሽ እንዲያገኙ አሸናፊና ገዥ ሀሳቦችን መቀበል ይገባል

ጎባ፣ ጥር 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የቆዩ አለመግባባቶችና የተሳሳቱ ትርክቶች በሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ 'የኔ ሀሳብ ብቻ' ከሚለው ያረጀ አስተሳሰብ በመውጣት አሸናፊና ገዥ ሀሳቦችን መቀበል እንደሚገባ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራን አመለከቱ፡፡ 

በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታሰበው ብሔራዊ የምክክር መድረክ ችግሮችን በዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል መደላደል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።

"ምክክሩ ለእውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መደላድል የሚፈጥር በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ  ይገባል" ሲሉ ምሁራኑ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

መንግስት የተወሰኑ ግለሰቦችን ክስ እንዲቋረጥ በማድረግ ከእስር መፍታቱ ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑንም ምሁራኑ አመልክተዋል፡፡

ዶክተር ከፍያለሁ ተሰማ እንዳሉት፤ በአገሪቱ የቆዩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ካለመመካከርና ለዘመናት በተዘሩ የተሳሳቱ ትርክቶች አማካይነት የተፈጠሩ ናቸው፡፡

"የኢትዮጵያ ህዝብ የማህበረሰብን ችግሮች የሚፈታበት የገዳ ስርዓትን ጨምሮ ሌሎች የራሱ የሆነ ቱባ እሴት ያለው ነው" ያሉት በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ስነተግባቦት መምህርና ተመራማሪ አቶ ኡመር መሐመድኑር፤  የቆየ ባህላዊና አካታች ስርዓት ያለው ማህበረሰብ ችግሮቹን ተቀራርቦ በሰከነና በሰለጠነ መንፈስ በመነጋገር እንደሚፈታ ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክር መድረክ እንዲካሄድ መወሰኑ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር የተሻለ አማራጭ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የቋንቋና ስነጽሁፍ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መሐመድ ጀማል ናቸው።

የምክክር መድረኩ አካታችና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ሊተኮርበት እንደሚገባ መክረዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃንም የምክክር መድረኩን አስፈላጊነትና ዓላማ ህዝቡ እንዲረዳው በስፋት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

"የምክክር መድረኩ በኢትዮጵያ እውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት ምቹ መደላድል የሚፈጥር በመሆኑ ለስኬታማነቱ ምሁራን የድርሻችንን እንወጣለን" ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም