የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ዘላቂ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ዘላቂ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ ነው

አዳማ ጥር 19/2014 (ኢዜአ) የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ከአስቸኳይ ጊዜ ህክምና በኋላ ዘላቂ ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ።
የመንገድ ደህንነትና የመንገድ ፈንድ አገልግሎት ከጤና ጥበቃ፣ ከክልሎች የጤና ቢሮዎች፣ በየደረጃው ከሚገኙ የፖሊስ ኮሚሽኖችና የዘርፉ ሴክተሮች ጋር በስርአቱ አተገባበር ላይ መክሯል።
በትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር የመንገድ ደህንነትና የመድን ፈንድ አገልግሎት ሃላፊ አቶ ጀማል አባሶ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ከአስቸኳይ ጊዜ የህክምና እርዳታ በኋላ ቀጣይ ህክምና በማጣት ለህልፈተ ህይወት ይዳረጋሉ።
"ተጎጂዎች እስከ 2ሺህ ብር በሚደርስ ወጭ የነጻ የአስቸኳይ ጊዜ ህክምና የሚያገኙ ቢሆንም ዘላቂ ህክምና ባለማግኘታቸው ለህልፈት ይዳረጋሉ" ብለዋል።
ለዚህም ተጎጂዎች ዘላቂ የተመላላሽና የተኝቶ መታከም አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል።
"አብዛኛው ማህበረሰብ ድንገተኛ የተሽከርካሪ አደጋ ሲገጥመው በእጁ ላይ ገንዘብ ስለማይኖር ዘላቂ ህክምና አያገኝም" ያሉት አቶ ጀማል "ተጎጂው ህይወቱ ካለፈ በኋላ ካሳ ከመክፈል ህይወቱን ማትረፍ ወሳኝ በመሆኑ የአሰራር ማሻሻያ ተደርጓል" ብለዋል።
ለአንድ ሰው በተሽከርካሪ አደጋ ህይወቱ ካለፈ በኋላ በሚከፈለው ካሳ ዙሪያ ያለውን የአሰራር ማሻሻያ በማድረግ እንዲሁም ተጎጂዎች ዘላቂ ህክምና እንዲያገኙና ህይወታቸውን ማትረፍ የሚያስችል አተገባበር እውን ለማድረግ የሚያስችል ስርአት እየተዘረጋ ይገኛል ነው ያሉት።
ከዚህ ቀደም ለተጎጅዎች እስከ 2ሺህ ብር የወጭ ሽፋን ይደረግ ከነበረው የአስቸኳይ ጊዜ የህክምና እርዳታ ክፍያ በተጨማሪ እስከ 40ሺህ ብር ወጭ የሚደረግበት የተመላላሽና የተኝቶ ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አዲስ አሰራር እየዘረጋን ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
አዲሱ አሰራር የተጎጂዎች መረጃ ከፖሊስና ከጤና ተቋማት በወቅቱ ያለመድረስ ክፍተትን የሚፈታ መሆኑንም አመልክተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ከ230 በላይ የሚሆኑ የመንግስትና የግል ጤና ተቋማት የአስቸኳይ ጊዜ የህክምና እርዳታ አገልግሎት በመስጠት ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ የህክምና ወጪ ሽፋን መደረጉን ሀላፊው አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ የመድን ፈንድ አገልግሎት ኤጄንሲ ስራ አስኪያጅ ኮማንደር አበበ አበራ በበኩላቸው በከተማዋ ከ140 በላይ በሚሆኑ የጤና ተቋማት ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጅዎች የአስቸኳይ ጊዜ ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

"አዲሱን አሰራር ውጤታማ ለማድረግ ፖሊስ አደጋ ሲደርስ በጥራትና በፍጥነት ሊያደርሰን ይገባል" ብለዋል።
"በተለይ በፖሊስና በህክምና ተቋማት መካከል ያለው ቅንጅት እጅጉን መሻሻል አለበት" ያሉት ሃላፊው ለዚህም አዲሱ አሰራር የአተገባበር የመግባቢያ ሰነድ የጎላ ሚና አለው" ሲሉ አመልክተዋል።
"በተሽከርካሪ ተጎጂዎች ላይ ካለው የችግሩ ስፋት አንፃር ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ ሰፊ ስራዎችን እየሰራን ነው" ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የድንገተኛ ህሙማን ቡድን አስተባባሪ ወይዘሮ ክበበ ጌራወርቅ ናቸው።

"ተጎጂዎች ከአስቸኳይ የህክምና ዕርዳታ ጀምሮ ዘላቂ ህክምና እንዲያገኙ ለማስቻል አዲሱ የአሰራር ማሻሻያ ቁልፍ ሚና አለው፣ "ከሆስፒታሎች ጀምሮ እስከ ጤና ጣቢያዎች ድረስ ወርደን የግንዛቤ ስራ እየሰራን ነው" ሲሉ አስታውቀዋል።