በኢትዮጵያ የታየውን አንድነትና የአሸናፊነት ድል በማጠናከር ለዘላቂ ልማትና ሰላም መትጋት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የታየውን አንድነትና የአሸናፊነት ድል በማጠናከር ለዘላቂ ልማትና ሰላም መትጋት ይገባል
ጥር 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኢድሪስ ሙሐመድ በኢትዮጵያ አሁን የታየውን አንድነትና የአሸናፊነት ድል በማጠናከር ለዘላቂ ልማትና ሰላም መትጋት እንደሚገባ ተናገሩ።
በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በጋምቤላ ክልል ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ጋምቤላ ከተማ ገብተዋል።
ዳያስፖራዎቹ በጋምቤላ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኢድሪስ ሙሐመድ ለተደረገተላቸው አቀባበል አመስግነው፥ ጋምቤላ ሲገቡ ያዩት ሰላምና የህዝቦች አንድነት እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አሁን የታየውን አንድነትና የአሸናፊነት ድል በማጠናከር ለዘላቂ ልማትና ሰላም መትጋት ይገባል ብለዋል።
ከአሜሪካ ቦስተን የመጡት ወይዘሮ ራሄል ፍቅርአብ አሜሪካ በነበሩበት ወቅት ኢትየጵያ እንደፈረሰች ተደርጎ ሲወራ እንደነበር አስታውሰው፤ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ባደረጉት ጉብኝት አሸባሪው ህወሃት በአፋርና በአማራ ክልሎች ከፍተኛ ጉዳት ቢያደርስም ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን ማረጋገጥ መቻላቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ልጆቿ እያሉ መቼም አትፈርስም ያሉት ወይዘሮ ራሄል፥ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ ሰላምና ልማት የጀመሩትን ትግል አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው ጉዳይ አሳስቧቸው በአካል በመገኘት እያደረጉ ላለው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።
ዳያስፓራዎች በሚኖራቸው ቆይታ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የመስህብ ሥፍራዎችና የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ጉብኝትና ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼