የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን በተለመደው ኢትዮጵያዊ መስተንግዶ ልንቀበል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን በተለመደው ኢትዮጵያዊ መስተንግዶ ልንቀበል ይገባል
አዲስ አበባ ጥር 19/2014(ኢዜአ) የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ህዝቡ በተለመደው ኢትዮጵያዊ መስተንግዶ ተቀብሎ እንዲያስተናግድ ጥሪ ቀረበ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ከቀናት በኋላ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
መደበኛ ጉባኤው በኢትዮጵያ እንዳይካሄድ የተለያዩ ጫናዎች ሲደረጉ ቢቆዩም በጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ በአፍሪካ መዲና እንዲካሄድ ተወስኗል ብለዋል።
በመሆኑም የጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄድ ያለውን ጠቀሜታ ሕዝቡ ተረድቶ እንግዶቹን በኢትዮጵያዊ መስተንግዶ እንዲቀበል ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በአዲስ አበባና ዙሪያ እንዲሁም በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ያሉ ሁሉ እንግዶችን ለመቀበል እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎች ወደተሟላ መደበኛ እንቅስቃሴ እየገቡ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አሁንም በመልሶ ግንባታ ረገድ ብዙ ስራ የሚጠበቅ በመሆኑ ሕዝቡ ትብብሩን ማጠናከር አለበት ብለዋል።
ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተፈናቃዮች መካከል እስካሁን 1 ነጥብ 2 የሚሆኑት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በድርቅ ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችንም ሕዝቡ ተረባርቦ ማገዝ እንዳለበት ነው ሚኒስትሩ ያሳሰቡት።
ለስድስት ወራት የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የቆይታ ጊዜ እንዲያጥር መንግስት መወሰኑንም ጠቁመዋል።
መንግስት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ስጋቶች በመቀነሳቸው ችግሮችን በመደበኛ የሕግ ማስከበር አካሄድ መቆጣጣር ስለሚቻል መሆኑን አብራርተዋል።
አገር አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳው አሸባሪው ሕወሓት በአፋርና በተወሰኑ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች አሁንም ትንኮሳ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ ትንኮሳም ወደ ትግራይ ይሄድ የነበረ የእርዳታ እህልና መድሃኒት ወደ ክልሉ እንዳይገባ አግዷል ነው ያሉት።
ቡድኑ ረሃብን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ እየተጠቀመ ለትግራይ ህዝብ ምንም ደንታ የሌለው መሆኑን በተግባር እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት አሸባሪው ሕወሓት የሚያደርገውን ትንኮሳ የመመከት ሙሉ አቅምና ዝግጅት ያለው ስለመሆኑም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።