35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ሁሉንም ፈተናዎች በድል ተሻግራ የቀጠለች መሆኗን ለአለም የምናሳይበት ይሆናል - ኢዜአ አማርኛ
35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ሁሉንም ፈተናዎች በድል ተሻግራ የቀጠለች መሆኗን ለአለም የምናሳይበት ይሆናል
ጥር 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ መካሄዱ ለኢትዮጵያ ታላቅ የዲፕሎማሲ ድል ከመሆኑ ባሻገር ኢትዮጵያ ሁሉንም ፈተናዎች በድል ተሻግራ የቀጠለች ሀገር መሆኗን ለመላው አለም የምናሳይበት ጉባኤ ይሆናል ሲል መንግስት አስታወቀ።
የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ የህዝብን ዘላቂ ሰላም፣ ጥቅምና የብልጽግና ጉዞ እውን መሆን የሚያረጋግጡ አለም አቀፍ ሁነቶችን ለማዘጋጀት እየተሰናዳች ትገኛለች ብለዋል።
በሚቀጥለው ሳምንት የሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤም የዚሁ ሁነት አካል መሆኑን ገልጸዋል።
ጉባኤው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ከተቋረጠበት ሁለት አመት በኋላ የሚካሄድ መሆኑን አውስተው፤ “ጉባኤው እንዳይካሄድ ቢፈለግም የህብረቱ መሪዎች ጉባኤው የሕብረቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ እንዲካሄድ ማድረጋቸቸው ለኢትዮጵያ ያላቸውን አጋርነት ያሳዩበት ነው” ብለዋል።
ይህ ውሳኔም ለኢትዮጵያ ታላቅ የዲፕሎማሲ ድል ነው ሲሉ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ “ኢትዮጵያ ሁሉንም ፈተናዎች በድል ተሻግራ የራሷን ችግሮች በራሷ ፈታ የቀጠለች ሀገር መሆኗን እንዲሁም ሰላምና መረጋጋቷን ለመላው አለም የምናሳይበት ጉባኤ ይሆናል” ብለዋል።
የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት አለም አቀፍ ጉባኤዎች እንዳይካሄዱ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዳይጎበኙና ሌሎችም ሁነቶች እንዳይደረጉ ጫናዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች ግን ጫናውን ወደ ጎን በመተው ጉባኤው በሕብረቱ መርህ መሠረት በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰናቸው ኢትዮጵያ ለህብረቱ ያበረከተችውን አስተዋጸኦ ዋጋ የሰጠ ነው በማለትም ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ለተሳታፊዎች የአገሪቱን ወጎችና ባህሎችን የጠበቀ የእንግዳ አቀባበል እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
የአካባቢን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች እንደዚህ ቀደሙ የተጠናከረ ትስስር እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል።