ሳንቴ ግሩፕ 100 የመተንፈሻ መሳሪያዎችን ለጤና ሚኒስቴር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ሳንቴ ግሩፕ 100 የመተንፈሻ መሳሪያዎችን ለጤና ሚኒስቴር ድጋፍ አደረገ
ጥር 18 /2014 (ኢዜአ) ሳንቴ ግሩፕ የተባለ አንድ የውጭ ኩባንያ 100 የመተንፈሻ ድጋፍ መሳሪያዎችን (ቬንትሌተር) ለጤና ሚኒስቴር ድጋፍ አደረገ።
የመተንፈሻ መሳሪያዎቹ በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ በሳንቴ ግሩፕ ሲከናወን በሞደርን ኢቲኤች ኩባንያ፣ አልፋ ትሬዲንግና ሌሎች አጋር አካላት ደግሞ የማጓጓዣ ወጪውን መሸፈናቸው ታውቋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ የተደረገው ድጋፍ ትልቅ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት የተጎዱ የጤና ተቋማትን ለማቋቋምና የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ሚኒስቴሩ ከአጋር አካላት ጋር እየሰራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ አገር ወዳድ ዜጎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ለጤናው ዘርፍ እገዛ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው 100 የመተንፈሻ መሳሪያዎችን ድጋፍ ላደረገው ሳንቴ ግሩፕ እንዲሁም የመጓጓዣ ወጭውን ለሸፈኑት ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።
የተደረገው ድጋፍ በተለይም በጦርነቱ ዘረፋና ውድመት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ለማጠናከር ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
በቀጣይም የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከልና በጦርነት የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሁሉም ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የሞደርን ኢቲኤች ኩባንያ የቴክኖሎጂ ክፍል ሃላፊ አቶ ታዲዮስ ተፈራ፤ የመተንፈሻ መሳሪያ ተደራሽነት በተለይም ለኮቪድ19 ህክምና ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በምታደርገው ጥረት ለመደገፍ ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።