ቀጥታ፡

በመላው ዓለም የሚገኘው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሳይዘናጋ ትግሉን መቀጠል አለበት

አዲስ አበባ፣ ጥር 18/2014/ኢዜአ/ በመላው ዓለም የሚገኘው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገር ባገኘችው ድል ሳይዘናጋ ትግሉን መቀጠል፤ አገሩንም በመደገፍ ከድህነት ማውጣት ይጠበቅበታል ሲሉ የዳያስፖራ አባላት ተናገሩ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ከእንግሊዝ፣ ከአሜሪካ እና ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ያልተቋረጠ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት የሰሙትና በአገር ቤት ቆይታቸው የተመለከቱት ፈጽሞ የተለያየ ሁኔታ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከአሜሪካ ሜሪላንድ የመጣችው ወጣት ሃና ወልደአማኑኤል እና ከእንግሊዝ ለንደን የመጡት ወይዘሮ ሶስና ተፈራ ስለ አገራቸው ሲሰሙ የቆዩትና በአካል ተገኝተው ያዩት እውነታ የማይገናኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን የተመለከቱ ከእውነት የራቁ አሉባልታዎች የሚሰራጩት መልካም ገጽታዋን ለማጥፋት በመሆኑ ዳያስፖራው አገሩን በመደገፍ ከድህነት ለማውጣት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ዳያስፖራው ከመንግስት ጎን በመቆም ለአገር ሠላምና ልማት አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅበታል ያሉት ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ስዌቶ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ መሪዎች አቶ አብነት ዘለቀ እና አቶ ተመስገን አቦ ናቸው።

የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ በማቋቋምና የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት ረገድ ዳያስፖራው ለአገሩ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም