ቀጥታ፡

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለዲፕ ካማራና የስራ ባልደረቦቻቸው ሞት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኢትዮጵያ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ዲፕ ካማራና የስራ ባልደረቦቻቸው ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጸ። ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በኢትዮጵያ በሚገኘው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅና ሁለት የስራ ባልደረቦቻቸው በደረሰባቸው ግድያ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን መግለጹን አስታውቋል። ለሟቾች ቤተሰቦች እንዲሁም ለመላው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ሰራተኞች መፅናናትን ተመኝቷል። ኮሚሽኑ ለዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የማያቋርጥ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጿል። የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ትልቅና ተጫባጭ ከሚባሉ የኢንቨስትመንት ስራዎች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀስና ከሚሰራው ስራ በላፈ የማህበራዊ ሃላፊነትን በአግባቡ እየተወጣና ፋብሪካው ባለበት አካባቢ ከሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መልካም ትስስር መፍጠሩን በመግለጫው ተጠቅሷል። ግድያው በተሰወነ በውጭ አገራት የኢንቨስትመንት ማህበረሰብና በኛ ላይም ቢሆን መረበሽ እንደሚፈጥር ከግንዛቤ ሊገባ እንደሚገባም ገልጿል ኮሚሽኑ። ጥቃቱ ያልተጠበቀ ክስተት እንደሆነና ቀጣይ መሰል ጥቃቶች እንዳያጋጥሙ የሚመለከታቸው አካላት ጠንክረው መስራት እንደሚገባቸው ኮሚሽኑ አስታውቋል። መንግስት ለባለሀብቶች የሚያስፈልገውን ድጋፍና ጥበቃ እንደሚያደርግም ጠቁሟል። መንግስትም ግድያውን የፈጸሙ አካላትን ይዞ ለህግ እንደሚያቀርብ ኮሚሽኑ ያለውን እምነት ገልጿል። በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች የሚገኙ ኢንቨስተሮች ደህንነት እንዲጠበቅ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል ተቋማት ጋር እንደሚሰራም አመልክቷል። በኢትዮጵያ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ አሁን ያሉበትን ሀዘን ተቋቁመው እንዲያልፉና ፋብሪካው "የአፍሪካን እድገት በመጨመር ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት ከፍተኛ አገር በቀል የኢንዱስትሪ ተቋማት የመፍጠር" ራዕዩን እንዲያሳካ በትብብር እንደሚሰራም መግለጫው አትቷል። የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን አደኣ በርጋ ወረዳ የሚገኝ ነው። ከሶስት ዓመት በፊት ስራውን የጀመረው ፋብሪካው ሲሚንቶ የማምረት አቅሙ በኢትዮጵያ ትልቁ ነው። በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን አደኣ በርጋ ወረዳ በሚገኘው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ዲፕ ካማራና ሁለት የስራ ባልደረቦቻቸው ትናንት ባልታወቁ የታጠቁ ሰዎች በተፈፀመባቸው ጥቃት ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው። በአሁኑ ወቅት መንግስት ግድያውን የፈጸሙ አካላትን ለመያዝ ጥብቅ ክትትል በማድረግ ላይ እንደሆነና ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ በሚደረገው ጥረትም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ መጠየቁም ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም