የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

ጥር 18 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ጉዳት ለደረሰበት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ።
ኢዜአ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ላፕቶፕ ኮምፒተሮች እንዲሁም ለአንድ ዓመት ነጻ የዜና አቅርቦት በድምሩ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።
በድጋፍ ርክክቡ ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እና የተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የላፕቶፕ ኮምፒዩተር ድጋፉን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ አስረክበዋል።
የመንግሥት የኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በዚህ ወቅት አሚኮ ሕዝቡ አሸባሪውን የህወሓት ወራሪ በተደራጀ መንገድ እንዲመክት ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው ተቋሙ በአሸባሪው ህወሓት ከደረሰበት ዘረፋና ውድመት አገግሞ ወደ ሥራ ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት የሚዲያ ተቋማት እያደረጉለት ያለው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአገሪቷ በተፈጠሩ ትርክቶች ምክንያት የተፈጠሩ ልዩነቶች እንዲጠቡና የአገር ግንባታ ሂደቱ እንዲቃና የሚዲያ ተቋማት በጋራ መስራት እንዳለባቸውም በማስገንዘብ "ለግጭት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት አካታች አገራዊ ምክክር እንዲደረግ ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑንና የሚዲያ ተቋማትም ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለመፍጠር በጋራ ሊሰሩ ይገባል''።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤ አሚኮ ኢትዮጵያዊነት እንዲጎለብትና በዜጎች መካከል መቀራረብ እንዲፈጠር ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የሚያከብረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ካለው ላይ ቀንሶ ለአሚኮ ያደረገው ድጋፍ ወንድማማችነትን የሚያጠናክር ነው ያሉት ዶክተር ቢቂላ ድጋፉ ተቋማቱ ለጋራ ዓላማ የሚሰሩ በመሆናቸው የራስን ሚዲያ እንደማጠናከር ነው በሚል የተደረገ በመሆኑ ኢዜአ ሊመሰገን ይገባል መደጋገፍ ለሌሎች ተቋማትም ዓርአያ ይሆናል ብለዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በምስራቅ አማራ የሚገኙ የተቋሙን ከስድስት በላይ የሬዴዮ ማሰራጫና አገልግሎት መስጫዎች ማውደሙን ገልጸዋል።
ይሁንና ሚዲያውን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት በተከናወኑ ተግባራት አብዛኞቹ ማሰራጫዎች ወደ ሥራ መመለስ መቻላቸውን ነው ተናግረው ተቋሙን ወደ ሥራ ለመመለስ ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን ካሳዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት መካከል ኢዜአ አንዱ መሆኑን በመጥቀስ መስጋና አቅርበዋል።
በዚህ መደጋገፍ የተገኘው ውጤት አገራዊ አንድነትን በማጠናከር ሂደትም ሊደገም ይገባል ሲሉም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤም ኢዜአ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ የሁለቱን ተቋማት ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
ኢዜአ ባለፉት 80 ዓመታት በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ጋር በርካታ ውጣ ውረዶችን በጋራ ያለፈ መሆኑንም አውስተዋል።