በከተማዋና አካባቢዋ በቴሌኮም የመስመር ሽቦ ላይ በተፈጸመ ስርቆት ከ10ሺህ የሚበልጡ የተቋማት አገልግሎት ተቋርጧል፤ ተስተጓጉሏል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋና አካባቢዋ በቴሌኮም የመስመር ሽቦ ላይ በተፈጸመ ስርቆት ከ10ሺህ የሚበልጡ የተቋማት አገልግሎት ተቋርጧል፤ ተስተጓጉሏል
ፍቼ፣ ጥር 18/2014 /ኢዜአ/ በፍቼ ከተማና አካባቢዋ በቴሌኮም የመስመር ሽቦ ላይ በተፈጸመ ስርቆት ከ10ሺህ የሚበልጡ የተቋማት አገልግሎት መቋረጡንና መስተጓጎሉን ኢትዮ-ቴሌኮም አስታወቀ።
የኢትዮ -ቴሌኮም የፍቼ አካባቢ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ደግሰው ተስፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት በተደጋጋሚ በመስመር ሽቦ ላይ በተፈጸመ ስርቆት የግል፣ የመንግስትና የድርጅት ደንበኞችአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር ፈጥሯል።
በመደበኛ ስልክ ፣ በፋክስና በኢንተርኔት አገልግሎቶች ላይ የመቋረጥና የመስተጓጎል ችግር ማጋጠሙን አብራርተዋል።
ከደንበኞች አገልግሎት መቋረጥ በተጨማሪ በተቋሙ ገቢ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
"በፅህፈት ቤቱ የቴክኒክ ቡድን አማካኝነት በየወቅቱ በመስመር ሽቦዎች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጥገና ተጓዳኝ ስራዎች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በአንድ ቀን አዳር የተጠገኑ መስመሮች ላይ ተመሳሳይ ስርቆት ስለሚፈጸም ችግሩን አዳጋች አድርጎታል"ብለዋል ።
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝተው አገልግሎት ላይ የዋሉ የመስመር ሽቦ ገመዶች ላይ በተደራጁ ሃይሎች ስርቆቱ ይፈፀማል የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው ጠቁመው በፖሊስ በኩል ክትትል እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ለቴሌኮም አገልግሎት ደህንነት መጠበቅ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የገለፁት ተወካዩ ህብረተሰቡ በከፍተኛ ወጪ ለተገነቡ መስመሮች ተገቢውን ጥበቃና ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
"በአንዳንድ ግለሰቦች የቴሌኮም የመስመር ሽቦን በመቁረጥ በድብቅ ለኤሌትሪክ አገልግሎት የመጠቀምን ጨምሮ በዘርፉ የሚፈጸም ወንጀል ስለመኖሩ በተደረገ ድንገተኛ አሰሳና ፍተሻ ተረጋግጧል" ያሉት ደግሞ የፍቼ ከተማ ፖሊስ ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ዋና ሳጅን አለሙ ባልቻ ናቸው።
በቴሌኮም መስመር ሽቦ ስርቆት የተጠረጠሩ 21 ግለሰቦች ከነ-ኤግዝቢቱ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፖሊስና በአቃቤ ህግ እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።
በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ወንጀለኞችን አጋልጦ የመስጠት ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆኑን በርካታ ክሶች እንዲዘጉ እያደረገ መሆኑም ሌላው ተግዳሮት እንደሆነ ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ የሚገለገልበትን የመንግስት ንብረት እንደራሱ በማየት በመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን ተደራጅቶ በመጠበቅ ሥርቆት የፈፀሙትን አሳልፎ ለህግ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
ፖሊስ በአሁኑ ወቅት የከተማው ሕብረተሰብ ራሱንና አካባቢውን ከወንጀል ድርጊት እንዲጠብቅ ለማስቻል የማደራጀት ስራ ማካሄዱን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት የፍቼ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ አዲሱ ደስታ ያለ ቆጣሪ ኤሌክትሪክ በማንኛውም ገመድ መቀጠል ህገወጥ ድርጊት መሆኑን ጠቁመው ድርጊቱን ለመቆጣጠር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተከታተለ መሆኑን ተናግረዋል።
በቴሌኮም በመስመር ላይ በሚፈፀም ስርቆት ምክንያት መስሪያ ቤታቸው የኢንተርኔትና የመደበኛ ስልክ አገልግሎት እንደሚቋረጥበት ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፍቼ ቅርንጫፍ ሥራ እስኪያጅ አቶ አየለ አመኑ በበኩላቸው ባንኩ በሚጠቀምባቸው የቴሌኮም አገልግሎቶች በተደጋጋሚ መስተጓጎል እንደሚያጋጥም ጠቁመው በአገልግሎቱ መቋረጥ ባንኩ ለደንበኞች በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ተመሳሳይ መስተጓጎል እያስከተለ መሆኑን አመልክተዋል ።