አሸባሪው ህወሓት በለኮሰው ጦርነትና በሌሎች የጸጥታ ችግሮች አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጉዳት ደርሷል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት በለኮሰው ጦርነትና በሌሎች የጸጥታ ችግሮች አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጉዳት ደርሷል
ባህር ዳር፣ ጥር 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነትና በሌሎች የጸጥታ ችግሮች በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ አነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ማህበር አስታወቀ።
የማህበሩ 11ኛ አገር አቀፍ የማይክሮ ፋይናንስ ኮንፈረስን በባህር ዳር ከተማ አካሄዷል።
የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ከበደ እንደገለጹት፤ በአማራ እና አፋር ክልሎች አሸባሪው ህወሃት ፈጽሞት በነበረው ወረራና በሌሎች የጸጥታ ችግሮች አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ንብረታቸው ተዘርፏል፣ ደንበኞቻቸው ተሰደዋል፣ ንብረቶቻቸው ወድመዋል በዚህም በኢንዱስትሪው ውስጥ ትልቅ ጉዳት ደርሷል።
የጉዳቱን ደረጃ የሚያሳይ መረጃ ከሁሉም አባል ማህበራት እየተጠናከረ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የችግሩ ሰለባ የሆኑ ተቋማት መልሰው ተቋቁመው መደበኛ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ማህበሩ ሙያዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የማህበሩ አባላት በየአካባቢው ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማትና እንደ ሀገርም ለተደረገው የመልሶ ማቋቋም ጥሪ 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።