ደብረ ብርሃን ዩንቨርስቲ ያስገነባቸውን የጤና ሳይንስ ኮሌጅና የማስተማሪያ ሆስፒታል አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ደብረ ብርሃን ዩንቨርስቲ ያስገነባቸውን የጤና ሳይንስ ኮሌጅና የማስተማሪያ ሆስፒታል አስመረቀ

ደብረ ብርሀን ኢዜአ ጥር 17/2014 ... የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል በ700 ሚሊዮን ብር ያስገነባቸውን የጤና ሳይንስ ኮሌጅና የማስተማሪያ ሆስፒታል ዛሬ አስመረቀ ።
ዩኒቨርስቲው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በተገኙበት ያስመረቃቸው የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ መታሰቢያ የጤና ሳይንስ ካምፓስና የሐኪም ግዛው መታሰቢያ የማስተማሪያ ሆስፒታል ናቸው።
በዩኒቨርስቲው የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር የሺህ ሐረግ ጌታነህ በሥነስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ጤና ሳይንስ ካምፓሱ 44 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለ ስድስት ወለል፣ ባለሶስት ወለል ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት እና ባለሶስት ወለል የአስተዳደር ህንፃዎችን አካቶ የያዘ ነው።
ህንፃዎቹ በውስጣቸውም የሕክምና ቤተሙከራ፣ የተማሪዎች መኖሪያና መማሪያ ክፍሎችን፣ አዳራሾች ሌሎች ለመማር ማስተማር ስራው አጋዥ የሆኑ ክፍሎችን ያካተቱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ካምፓሱ ለስራ አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎችና ቁሳቁስ የተማሉለት ስለሆነ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ይጀምራል ብለዋል።
ለአገልግሎት ብቁ የሆነው የሐኪም ግዛው መታሰቢያ የማስተማሪያ ሆስፒታል ቀደም ሲል የነበረ ግንባታ ሲሆን ተሻሽሎ መገንባቱን አመልክተዋል።
ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የሕጻናት ሕክምና መስጫን ጨምሮ ወደ 200 የሚጠጉ አልጋዎች ሲኖሩት አሁን 140 ያህል አልጋዎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከማስተማሪያነት ባለፈ በአማራ፣ በኦሮሚያና በአፋር ክልሎች አጎራባች ወረዳዎች የሚገኙ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ያህል ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበርም መስተማሪያ ሆስፒታሉን ስራ ለማስጀመር ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የህክምና መገልገያ መሳሪዎችና ቁሳቁስ እንደተሟሉለትም አስረድተዋል።
የደብረ ብርሀን ከተማ ነዋሪ አቶ ጌታቸው መኮነን በሰጡት አስተያየት በዩኒቨርስቲው እየተከናወኑ ያሉ የ ልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ችግሮች እየፈቱ ነው ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት ዛሬ የተመረቁት ተቋማትም ለዩኒቨርስቲው ተጨማሪ አቅም ከመሆናቸው ባለፈ የአካባቢው ማህብረሰብ የተሟላ ሕክምና እንዲያገኝ የላቀ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
በሥነሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ፣ የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌውና ሌሎች የክልልና የፌደራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡