ቀጥታ፡

የመገናኛ ብዙሃን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማስታወቂያ ሲያሰራጩ የመረጃዎችን ትክክለኛነት በማረጋገጥ ሊሆን ይገባል

ጥር 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማስታወቂያ ሲያሰራጩ የመረጃዎችን ትክክለኛነት በማረጋገጥ ሊሆን እንደሚገባ የፌዴራል ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን አሳሰበ፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባስልጣን ከፌዴራል ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ጋር በመተባበር 'የማስታወቂያ ስርጭት ሁኔታ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት' በሚል ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በመድረኩ የፌዴራል ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም አድማሴ፤ እውቅና ሳይኖራቸው ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሚና ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማስታወቂያ ለማስተላለፍ በሚስማሙበት ወቅት አስፈላጊ የሚባሉ መረጃዎችን ሊይዙና ሊያረጋግጡ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛው ተስፋዬ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስታወቂያዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲሰራጩ የመረጃ ክፍተት እንደሚስተዋልባቸው ገልፀዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማስታወቂያዎች በሚያሰራጩበት ወቅት ምን አይነት መረጃዎች መሟላት እንዳለባቸው ማወቅ አለባቸው ብለዋል፡፡

በዚህ ዙሪያ የማሳወቅ እና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ከትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ጋር በመተባበር እየተሰራ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

የአሃዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ፤ የመገናኛ ብዙሃን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማስታወቂያ ከማሰራጨታቸው በፊት ወቅታዊ፣ ህጋዊና ተገቢ የሆኑ መረጃዎችን ልናጣራ ይገባል ብለዋል፡፡

አያይዘውም የትምህርት ስልጠና ባለስልጣንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያሰሩትን ማስታወቂያ መከታተል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም