የቤንች ሸኮ ዞን አሸባሪው ህወሃት ላፈናቀላቸው ዜጎች ድጋፍ ማሰባሰብ ጀመረ

72

ሚዛን፣ ጥር 17/2014(ኢዜአ) በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን አሸባሪው ህወሀት በከፈተው ጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የማሰባሰብ መርኃ ግብር ዛሬ ተጀምሯል።


"200 ብር ለእናቴ - አንድ እቃ ለአንድ ቤተሰብ" በሚል መሪ ቃል በተጀመረው የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርኃግብር ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና ዓይነት ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዷል።


በመርኃግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ መዓዛ ካሜቶ በአሸባሪው ህወሓት ወረራ በአማራና አፋር ክልሎች በርካታ ዜጎች ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።


ክልሉ በሽብር ቡድኑ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እያሰባሰበ መሆኑን አንስተው የቤንች ሸኮ ዞን ህዝብ ለተጎዱ ዜጎች የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።


እንደ ክልል በተለይ ሴቶች በሚያደርጉት ተሳትፎ 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብና 9 ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ ለመሰብሰብ ግብ መጣሉን ኃላፊዋ አስታውቀዋል።


በብልጽግና ፓርቲ የቤንች ሸኮ ዞን የርዕዮተ ዓለምና ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ስምኦን በበኩላቸው "የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም በሚካሄደው ሀገራዊ እንቅስቃሴ የመረዳዳት ባህልን ማጎልበትና ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ያስፈልጋል" ብለዋል።


በመርሀ ግብሩ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ የዞኑ የሴቶች አደረጃጀቶችና ሴት መንግሥት ሠራተኞች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም