ቀጥታ፡

በተያዘው ዓመት ከ100 ሺህ ሄክታር በሚልቅ የቡና ማሳ ጉንደላ /እደሳ/ ይከናወናል

አዲስ አበባ ጥር 17/2014(ኢዜአ) የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ በተያዘው ዓመት ከ100 ሺህ ሄክታር በሚልቅ የቡና ማሳ ጉንደላ /እደሳ/ እንደሚከናወን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጸ፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ300 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ ማሳ ያረጁ የቡና ዛፎች ላይ ጉንደላ /እደሳ/ ተከናውኗል።

የቡና ጉንደላ የቡና ተክል በእርጅና ምክንያት ምርት ሳይሰጥ ሲቀር ቅርንጫፎቹን በሳይንሳዊ መንገድ በመቁረጥ እንደ አዲስ እንዲበቅል የማድረግ ዘዴ ነው።

ቡና በሄክታር እስከ 21 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥ ቢታወቅም በኢትዮጵያ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ከቡና ማሳቸው በሄክታር የሚያገኙት ከአራት ኩንታል ያልዘለለ ምርት ነው።

ይህ የሆነው ለረጅም ዘመናት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የቡና ተክል በእርጅናና በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈለገውን ያህል ምርት መስጠት ባለመቻሉ መሆኑ ይነገራል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ከእርጅና ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የምርት መቀነስ ለመከላከል ስትራቴጂ ተነድፎ ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮም ጉንደላውን ለአራተኛ ጊዜ ለማከናወን ባለፈው ሣምንት ንቅናቄ በመፍጠር መጀመሩን ነው ዶክተር አዱኛ የገለጹት፡፡

ቡና ከተጎነደለና ከታደሰ በኋላ ተያይዘው የሚሰሩ ሥራዎች በአግባቡ ከተከናወኑ በሦስት ዓመት ውስጥ አዲስ ምርት ሊሰጥ እንደሚችልም ተናግረዋል።

በመሆኑም ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎችም ሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ድርሻቸውን በመውሰድ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ጉንደላውን ለማሳካት እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ሥራው በባለሥልጣኑ ብቻ የሚከወን ባለመሆኑ በቡና ላይ የሚሰሩ ማኅበራትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉንና ለጉንደላ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን እያቀረቡ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ፣ የደቡብ እና ሲዳማ ክልሎችም ከፍተኛ በጀት በመመደብ ለአርሶ አደሩ ግብዓቶቹ በጊዜ ደርሰው ጉንደላው በተያዘለት ጊዜ እንዲከናወን ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካላት 1 ሚሊዮን ሄክታር የቡና ማሳ 931 ሺህ ሄክታር ያህሉ ምርት የሚሰጥ ነው።

በአንድ ሄክታር በአማካይ ሰባት ኩንታል የቡና ምርት የሚገኝ ሲሆን ጉንደላውና ሌሎች ሥራዎች በአግባቡ ከተከናወኑ ደግሞ ሦስት እጥፍ ምርት እንደሚገኝ ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም