ባንኩ የደንበኞቹን ትክክለኛ ማንነት ለመለየት የሚያስችል የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ የደንበኞቹን ትክክለኛ ማንነት ለመለየት የሚያስችል የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 17/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞቹን ትክክለኛ ማንነት በቀላሉ መለየት የሚያስችል የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ባንኩ ስምምነቱን የተፈራረመው ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ጽህፈት ቤት ጋር ነው፡፡
የጽህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ዩዳሔ አርአያስላሴ እንዳሉት፤ በስምምነቱ መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ የባንኩ ደንበኞች የዲጂታል መታወቂያ የሚያገኙ ይሆናል፡፡
የዲጂታል መታወቂያ ስርዓቱን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ሁሉም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የደንበኞቻቸውን ማንነት በትክክል እንዲያውቁ ለማስቻል መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
የደንበኞችን ማንነት በትክክል ለመለየት የሚያገለግለው የቀበሌ መታወቂያ በቂ ሆኖ አለመገኘት ይህን ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአንድ ማንነት የተለያዩ ስሞችን በመጠቀም ሁለት እና ከዚያ በላይ መታወቂያ የማውጣት ህገ-ወጥነትን እንደሚከላከል ተገልጿል፡፡
የኢትየጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዘዳንት አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ህገ- ወጥነትን ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
በባንክ ውስጥ ትልቁ ስራ ደንበኛን ማወቅ ነው ያሉት ፕሬዘዳንቱ ፤ ከዚህ አኳያ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ደንበኞቻችንን በቀላሉ እንድናውቅ በማገዝ ስራችን ለማቅለል ያግዘናል ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ተግባራዊ መሆን የባንክ የአሰራር ስርዓትን በመቀየር ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡
ባንኮች ከዚህ በፊት ይህን አይነት የአሰራር ስርዓት ባለመከተላቸው ደንበኞቻቸው የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች በአግባቡ ሳይሰጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህን አሰራር ተግባራዊ ያደረጉ የአፍሪካ አገራት በደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ትልቅ ውጤት እንዳስመዘገቡም ነው ለአብነት ያነሱት፡፡