ቀጥታ፡

"አሸባሪው ህወሃት ያወደማቸውን ሀብትና ንብረቶች በትብብር መልሶ ለመገንባት መዘጋጀት አለብን"

ጥር 17/2014/ኢዜአ/ "አሸባሪው ህወሃት ያወደማቸውን ሀብትና ንብረቶች በትብብር መልሶ ለመገንባት መዘጋጀት አለብን" ሲሉ በጀርመን አገር የሚኖሩ አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሃት በተለይም በአፋርና አማራ ክልሎች በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በተለይም በህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋና ውድመት መፈፀሙ የሚታወስ ነው።

አሸባሪው ቡድን ከዘረፋና ውድመቱ በተጨማሪ በርካቶችን ከቀያቸው በማፈናቀል ለከፍተኛ ችግር ዳርጎ ቆይቷል።

የአሸባሪውን አረመኔያዊ ድርጊት በተለይም በውጭ አገር ይኖሩ የነበሩ በርካታ ዳያስፖራዎች ጉዳቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ በተለይም በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ሳቢያ የወደሙትን አካባቢዎች በመጎብኘት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።

የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው ከጀርመን ወደ አገር ቤት በመግባት አሸባሪው ህወሃት ጉዳት ያደረሰባቸውን አካባቢዎች ከጎበኙት ዳያስፖራዎች መካከል ወይዘሮ ሊያ መላኩ ይጠቀሳሉ።

በደሴና በተለይ የመቅደላ ማሻ በጎበኙበት ወቅት የተመለከቱት ውድመት የከፋ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ሊያ መልሶ የመገንባት አገራዊ ግዴታ አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያን ጥሪ በመቀበል ወደ ሀገር ሲገቡ ለወደሙ አካባቢዎች የሚውሉ የህክምና ቁሳቁሶችን ያስረከቡ ሲሆን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግም ቃል ገብተው የመጡ እንደሆነ አንስተዋል።

በመቅደላ አካባቢ በተለይ በህዝብ መገልገያ ሆስፒታል ላይ የደረሰውን ጉዳት በፎቶና በቪዲዮ በማስደገፍ  በጀርመንኛ ቋንቋ መረጃ እንደሰሩበት ገልጸዋል''።

ኢትዮጵያ ላይ በሽብር ቡድኑ የደረሰውን ጉዳት ለሌሎች ለማስረዳት በጀርመን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በየትኛውም ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የደረሰውን ውድመት መልሶ በመገንባት ሊረባረቡ ይገባል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሃት በወረራ በቆየባቸው የአማራና አፋር ክልሎች ከ35 በላይ ሆስፒታሎች፣ 418 ጤና ጣቢያዎች፣ 1 ሺህ 700 በላይ ጤና ኬላዎች ላይ ዘረፋና ውድመት መፈፀሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም