ፓርኩ ለአገርና ለድሬዳዋ ሁለንተናዊ ዕድገት ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጣ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ፓርኩ ለአገርና ለድሬዳዋ ሁለንተናዊ ዕድገት ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጣ መስራት ይገባል
ድሬዳዋ፣ ጥር 17/2014 (ኢዜአ) የድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለአገርና ለድሬዳዋ ሁለንተናዊ ዕድገት፣ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጣ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
የኮሚቴው አባላት በምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ያሉ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና ቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን እየጎበኙ ነው፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና የቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ አባላት በድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርክና በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባውንና ለ1 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ያስገኘውን የድሬድዋ ሞተርስ የባለሦስት እግር ተሽከርካሪ መገጣጠሚያን ተመልክቷል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብዱልጀዋድ መሐመድ እንደተናገሩት፤ፓርኩ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና የሥራ እድል በመፍጠር አበረታች ሥራ እየሰራ ቢሆንም ከተዋቀረበት ስትራቴጂክ ሥፍራ አንጻር የሚጠበቅበትን ውጤት እያመጣ አይደለም፡፡
ፓርኩ ለጅቡቲ ወደብ ያለው ቀረቤታ፣ ከወደቡ ጋር በባቡርና በአስፓልት መንገድ ከመገናኘቱ በተጨማሪ በደረቅ ወደብ አቅራቢያ መገንባቱ ካለው ተመራጭና ተፈላጊነት አንጻር አሁን በፓርኩ ከተገነቡ 15 ሼዶች ወደ ሥራ የገቡት 3 ብቻ መሆናቸው በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ችግሩን በመፍታት የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን ወደ ፓርኩ በማስገባት ሼዶቹ ሥራ እንዲጀምሩ በማድረግ ለድሬዳዋ ብሎም ለአገር የሚጠበቅበትን ጥቅም እንዲያስገኝ ባለሃብቶችን በመሳብ በኩል የፌደራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በቁርጠኝነት መሰራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የፓርኩን መሠረታዊ ችግሮች በመፍታት ድሬዳዋ የምስራቅ የኢትዮጵያ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከልነት እውን ለማድረግና አገራዊ የለውጥ ጉዞን ለማሳካት በፌደራልም ሆነ በአስተዳደሩ በኩል የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡
አቶ አብዱልጀዋድ አክለው "ከፓርኩ በተጨማሪ በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ መንደር ወደ ስራ የገቡ ባለሃብቶች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት አበረታች ተግባር ማከናወናቸው የሚበረታታ ነው" ብለዋል ፡፡
የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩልም ጥሩ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በፓርኩ ተገኝቶ ያካሄደው የሥራ ግምገማ ለቀጣይ ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን የሚያግዝ መሆኑን የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሚል ኢብራሂም ተናግረዋል።
በፓርኩ ሥራ የጀመሩ ባለሃብቶች ባለፉት ስድስት ወራት ከ2 ሺህ 300 በላይ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንና ወደ ውጭ ከላኳቸው ምርቶችም ከ3 ሚሊዮን 650 ሺህ በላይ ዶላር መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ‹‹ባለፉት ስድስት ወራት ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬ ማዳን ችለናል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ በቀጣዮቹ ቀናት በሐረሪና በሶማሌ ክልሎች ተመሣሣይ ጉብኝት እንደሚያደርግ ታውቋል።