የዳያስፖራውን ተሳትፎ የሚያጠናክር 'ኢ-ሰርቪስ' የተሰኘ የአገልግሎት መስጫ ስርዓት ይፋ ሆነ

26

ጥር 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያግዝ 'ኢ-ሰርቪስ' የተሰኘ የአገልግሎት መስጫ ስርዓት ይፋ ሆነ፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ከተለያዩ የዓለም አገራት ከመጡ የዳያስፖራ ተወካዮች ጋር ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ምክክር አድርጓል።

በመድረኩም ዳያስፖራው ካለበት ቦታ በአገሩ ጉዳይ ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ እንዲያደርግና መንግስታዊ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችለው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የበለጸገ የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት ይፋ ሆኗል፡፡

አሰራሩም በመንግስት የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ትኩረት የተሰጠው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ አካል ሲሆን የባንክ ሂሳብ መክፈት፣ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ማግኘት እንዲሁም የኢንቨስትመንትና ንግድ ስራዎችን ማቀላጠፍ የሚያስችሉ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ገልጿል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሃመድ እንድሪስ እንዳሉት፤ የአሰራር ስርዓቱ ዳያስፖራው ወደ አገሩ ከመምጣቱ በፊት ባለበት ሆኖ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው።

ኤጀንሲው የዳያስፖራው በፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ የሃብት ማሰባሰብ እንዲሁም  በእውቀትና ክህሎት ሽግግር ላይ እንዲሳተፍ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ በቀጣይም ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ያለውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

የዳያስፖራ ተወካዮች በበኩላቸው ወደ ሚኖሩባቸው አገራት ሲመለሱ በተፈጠረው ትስስር በመታገዝ ለኢትዮጵያ እድገት ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮ-ካናዳዊያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) ሊቀመንበር ዶክተር ትሁት አስፋው ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ለአገራቸው ሁለንተናዊ ለውጥ በጋራ እየሰሩ ቢሆንም በርካታ የቤት ስራዎች እንደሚቀሩ ጠቁመዋል።

የዳያስፖራው ተሳትፎ በአንድ ወቅት ሞቅ ብሎ የሚቀዘቅዝ ሳይሆን በተደራጀ መልኩ መቀጠል እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡

ዳያስፖራው አገሩን ለመደገፍ በተናጥል ከሚያደርገው ጥረት ይልቅ በተደራጀ መልኩ ቢንቀሳቀስ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆን የተናገሩት ደግሞ በኔዘርላንድ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አስተባባሪ ሻምበል ውብሸት ሙላቱ ናቸው፡፡

ከዚህ አኳያ ዳያስፖራው በጋራ በመሆን ለአገር ልማት የሚጠቅም ግዙፍ ፕሮጀክት መፍጠር እንደሚችልም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም