የኦሮሚያ የግብርና ሽግግር ምክር ቤት ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ የግብርና ሽግግር ምክር ቤት ተመሰረተ

አዳማ ጥር 16/2014(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል በግብርና ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ ተቋማዊ የሚያደርግ የሽግግር ምክር ቤት ተመሰረተ ።
በክልሉ ግብርናን ለማዘመንና በተቋማዊ አደረጃጀት ለመምራት አላማ ያደረገ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳና የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴንን ጨምሮ የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የተለያዩ ድርጅቶች ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።
በመድረኩ የክልሉ ግብርና ሽግግር ምክር ቤት በይፋ ተመስርቷል።

ምክር ቤቱ የፌዴራልና የክልሉ የግብርና ምርምር ማዕከላት፣ዩኒቨርሲቲዎችና የምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዞች፣በየደረጃው ያሉ የግብርና ሴክተሮችን በአባልነት ያቀፈ ነው።
ክልሉን በስንዴ፣ በገብስ፣ በጤፍ፣ በጥራጥሬ፣ በቡና፣ በአትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ በሰባት ክላስተሮች በማደራጀት በግብርና ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ሽግግር ለማሳካት ምክር ቤቱ መቋቋሙ ተመላክቷል።
የምክር ቤቱ መቋቋም የቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ መካናይዜሽን፤ መስኖ፣ የተሟላ የኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ የገጠር ፋይናንስ አቅርቦት፣ገበያ ተኮር ምርቶች፣ በምግብ ራስን መቻልና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማሳደግ አቅም እንደሚፈጥርም ተገልጿል።
ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካትና የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በምክር ቤቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሥራዎች መሆናቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱረህማን አብደላ አስታውቀዋል።