በጋሞጎፋ ዞን መለኮዛ ወረዳ የቤተክርስቲያን መገልገያ የነበረ ቦታ አለአግባብ በመነጠቁ ተቸግረናል...የእምነቱ ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞጎፋ ዞን መለኮዛ ወረዳ የቤተክርስቲያን መገልገያ የነበረ ቦታ አለአግባብ በመነጠቁ ተቸግረናል...የእምነቱ ተከታዮች
ሀዋሳ ነሀሴ 23/2010 በደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን መለኮዛ ወረዳ የለሃ ደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርሲቲያን የጥምቀት ቦታ አለ አግባብ ተወሰደብን ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታ አቀረቡ። የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ለጥያቄው ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን እንደሚልክ አስታውቋል። በጋሞ ጎፋ ዞን መለኮዛ ወረዳ የደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል ቤቴክርሲቲያን አስተዳዳሪ ቀሲስ ትዕዛዙ ደነቀ ለኢዜአ እንደገለጹት ቤተክርስቲያኗ ከ1962 ዓ.ም. ጀምሮ ትጠቀምበት የነበረው የጥምቀትና መስቀል በዓል ማክበሪያ ቦታ አላአግባብ ተወስዷል። እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ ቦታው ለ48 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ከተማው ካርታ ሲሰራለት ባለመካተቱ ቅሬታ ማቅረባቸውንና በስህተት አለመካተቱን የሚገልጽ መረጃ ከዞኑ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ አሁን በ2010 በድጋሚ የካርታ ክለሳ ሲደረግ ምላሽ ሳይሰጥ ቦታው መናኸሪያ ይሆናል በሚል መታጠሩንና ይህም አግባብ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጉዳዮን በተደጋጋሚ ለመንግስት አካላት አቅርበናል ያሉት አስተዳዳሪው ተገቢው ምላሽ አለመሰጠቱን ቤተክርሲትያኗም ለስምንት ወራት ተዘግታ መቆየቷንና አገልጋዮችም ለእስር ተዳርገው እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም የክልሉ መንግስት ጥያቄያቸውን እንዲመልስላቸውና በካርታና ፕላኑ ተካቶ ይዞታነቱ የቤተክርሲቲያኗ ሊሆን ይገባል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ የኦርቶዶክስ እምነት ተቋማት ከተሞች ፕላን ሳይዙ በፊት ጭምር የነበሩ መሆናቸው ከግንዛቤ እንዲገባና ተለዋጭ ቦታ ሳይሆን የቀደመው ይዞታ ሊሰጠን ይገባል ብለዋል፡፡ ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢና የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት የአካባቢው ነዋሪ አቶ አበራ ግርማ በበኩላቸው ቦታው ጥምቀትና መስቀልን ከማክበር ባለፈ የእምነቱ ተከታይ አባቶች መካነ መቃብር ያረፈበት ጭምር ነው ብለዋል። ቦታው ቤተክርሲቲያኗ ለረዥም ዓመታት ትጠቀምበት የነበረ ቢሆንም በተፈጠረው ችግር ምክንያት በ2010 ዓ.ም የጥምቀት በዓል ሳይከበር መቅረቱን ገልጸዋል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ ለክልሉ መንግስት ለማሳወቅ የእምነቱ ተከታይ የሆኑ 400 የሚጠጉ ሰዎች ቅሬታቸውን ለማሰማት ወደ ሃዋሳ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ “ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ህጋዊ የሆነ መንገድ እየተከተልን ነው” ያለው ደግሞ ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢና የአካባቢው ነዋሪ ወጣት በረከት ክፍሌ ነው፡፡ “በአካባቢው የተለያዩ እምነት ተከታተዮች በዓሉን ሲያከብሩ የኖሩበት ቢሆንም ከቤተክርስቲያኗ እውቅና ውጭ ለሌላ አገልግሎት እንዲውል መደረጉ አብሮ የኖረውን ህዝብ አንድነት የሚያጎድፍ ነው” ብሏል፡፡ በመሆኑም የክልሉ መንግስት ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ቦታው የቤተክርሲቲያኗ ይዞታ ሆኖ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ታመነ ተሰማ በጉዳዩ ላይ ለኢዜአ በሰጡት ምላሽ ከቅሬታ አቅራቢዎቹ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ሰፊ ውይይት አድርገዋል። እንደ አቶ ታመነ ገለጻ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ህጋዊ የይዞታ ቦታ ማረጋጋጫ እንዳላቀረቡና ቦታውን መንግስትም ለተለያዩ ሁነቶች ይጠቀሙበት እንደነበረ መናገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ተለዋጭ ቦታ ከዞኑ መንግስት እንደተሰጣቸው የተናገሩት አቶ ታመነ ጉዳዩን የሚያጣራ ከሚመለከተው አካል የተወጣጣ ቡድን በነገው እለት እንደሚንቀሳቀስ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ጉዳዩ የደረሰበትን ተከታትሎ መረጃ የሚያደርስ ይሆናል፡፡