በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ በሸኔ የታገቱ 6 ግለሰቦችን ለማስለቀቅ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የፌደራል የደኅንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ

99

ጥር 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሸኔ አምስት ተማሪዎችንና አንድ በንግድ ስራ የሚተዳደር ግለሰብን ጨምሮ በድምሩ ስድስት ሰዎችን በኦሮሚያ ክልል ማገቱን የፌደራል የደኅንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ታጋቾቹ ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ ሲጓዙ ምስራቅ ወለጋ ጎቡ ሰዮ ወረዳ ልዩ ስሙ ባፋኖ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰአት አካባቢ በሽብር ቡድኑ ታፍነው መወሰዳቸውን ግብረ ሃይሉ ለኢዜአ በላከው መግለጫው አመልክቷል፡፡

ከሽብርተኛው ህወሓት ጋር በመቀናጀት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ሽብርና ትርምስ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱት የሸኔ ቡድን ታጣቂዎች በፌደራል የደኅንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል እና በኦሮሚያ ፀጥታ አካላት በቅንጅት እየተወሰደባቸው ባለዉ እርምጃ እየተደመሰሱ መሆናቸውን መግለጫው ጠቁሟል።

ይሁንና የተበታተኑት የቡድኑ አንዳንድ ኃይሎች በየዋሻውና ጥሻው በመደበቅ በንፁሃን ላይ እንዲህ አይነት አስነዋሪ አፈናና እገታ መፈፀማቸውን የጋራ ግብረ ሀይሉ ገልጿል፡፡

የፌደራል የደኅንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ከኦሮሚያ ክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ታጋቾችን የማስለቀቁ እንቅስቃሴም እየተካሄደ በመሆኑ፤ እርምጃዎችን ተከትሎ የሚገኘውን ውጤት በቀጣይ ለህዝቡ እንደሚያሳወቅ በመግለጫው አረጋግጧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም